ወጣቶች በግንባር ቀደምነት ለሰላም ዘብ ሊቆሙ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች በግንባር ቀደምነት ለሰላም ዘብ ሊቆሙ ይገባል

ባህር ዳር፤ ህዳር 21 /2016 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እየተደረገ ባለው የተቀናጀ ጥረት ወጣቶች በግንባር ቀደምትነት ለሰላም ዘብ ሊቆሙ እንደሚገባ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ጋሻው ተቀባ ገለጹ።
“ድንበር ተሻጋሪ የወጣቶች እንቅስቃሴ ለፓን አፍሪካኒዝም” በሚል መሪ ሃሳብ 17ኛ የአፍሪካ ወጣቶች ቀን በባህር ዳር ከተማ ዛሬ ተከብሯል።
የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ጋሻው ተቀባ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ ለአንድ አገር ሁለንተናዊ እድገት ሰላም ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ባጋጠመው የጸጥታ ችግር በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩን አውስተው፤ ለዘላቂ መፍትሄው ወጣቶች በተደራጀ አግባብ መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በተለይም አስተማማኝ ጸጥታ ለማስፈን መንግስት በተቀናጀ አግባብ እያደረገ ያለውን ጥረት በመደገፍ ወጣቶች በግንባር ቀደምትነት ለሰላም ዘብ መቆም እንደሚገባቸው አመልክተዋል።
ሃገር የምትገነባው በወጣቶች የበሰለ ሃሳብና ተግባር እንደሆነ ጠቅሰው፤ አሁን ላይ በክልሉ እየተስተዋለ ያለው ችግር እንዲፈታ በባለቤትነት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት ትምህርት ክፍል መምህርና ጽሁፍ አቅራቢ ዶክተር ፍቅርተ አዱኛ እንደገለጹት፤ ወጣቶችን ወደ አመራርነት በማምጣት የሰላም ተዋናይ እንዲሆኑ መስራት ያስፈልጋል።
ወጣቶች የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ባህል በማዳበር መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም አብራርተዋል።
እንደ አማራ ክልል ወጣት በተለይም በዚህ ወቅት ሰለ ሰላም በስፋት መስራት የሚጠይቅበት ወቅት መሆኑንም ገልጿል።
ሰላምን ለማረጋገጥ መንግስት ከሚያከናውናቸው ተግባራት ጎን ለጎን የወጣቶች ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ የገለጸችው ደግሞ ወጣት አኒሻ ወርቁ ናት።
ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን ወጣቶች ሚናቸው የጎላ መሆኑን ጠቅሳ፤ ወጣቶች የሚያነሷቸውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ መፍታት እንዳለበትም ጠቁማለች።
በባህርዳር በተከበረው የአፍሪካ ወጣቶች ቀን መረሃ ግብር ላይ የከተማ አስተዳደሩ የአመራር አባላትና የከተማው ወጣቶች ተሳታፊ ሆነዋል።