የኢንዱስትሪውን ፍላጎት በአግባቡ የተረዱ ባለሙያዎችን ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢንዱስትሪውን ፍላጎት በአግባቡ የተረዱ ባለሙያዎችን ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 21/2016 (ኢዜአ)፡- የኢንዱስትሪውን ፍላጎት በአግባቡ የተረዱ ባለሙያዎችን ለማፍራት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ለቴክኒክና ሙያ አሰልጣኞች በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪና በኤሌክትሮ ቴክኖሎጂ ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና ተጠናቋል።
ሥልጠናው በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪና ኤሌክትሮ ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን ከ15 የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የተውጣጡ 58 ሰልጣኞች ተሳትፈዋል።
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥልጠናና የተቋማት አቅም ግንባታ ሥራ አስፈጻሚ ሙህዲን አባሞጋ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የኢንዱስትሪውን ፍላጎት በአግባቡ የተረዱ ባለሙያዎችን ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህንንም ተከትሎ ይህ የአሰልጣኞች ሥልጠና መዘጋጀቱን ጠቁመው ሥልጠናው በኢንዱስትሪ ውስጥ ያለውን ከባቢ በደንብ የተረዳ አሰልጣኝ ለማብዛትና በሰልጣኝና ገበያው በሚፈልገው የባለሙያ አይነት መካከል ክፍተት እንዳይፈጠር ያስችላል ነው ያሉት።
ከዚህ ቀደም 500 የሚሆኑ ሰልጣኞች በተመሳሳይ ሥልጠና መውሰዳቸውን ገልጸው ይህ ሥልጠና በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በጀርመን የልማት ተራድኦ ድርጅት (ጂ አይ ዜድ) የኢትዮ-ጀርመን የትምህርትና ሥልጠና መርሃ-ግብር አስተባባሪ አሊ ሙሃመድ ካሃን በበኩላቸው ሥልጠናው በጀርመን መንግሥትና በአውሮፓ ኅብረት የገንዘብ ድጋፍ የሚከናወን መሆኑን ገልጸዋል።
መሰል የተግባር ሥልጠናዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው ለዚህም የሁሉም አካላት የጋራ ጥረት ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።
ከሥልጠናው ተሳታፊዎች መካከል በንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ አሰልጣኝ ምስጋና በላይ፤ ሥልጠናው ቀደም ሲል በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ያላትን እውቀት በተግባር ያየችበት መሆኑን ገልጻለች።
በቀጣይም ከዚህ ሥልጠና ያገኘችውን እውቀት ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች።
ሌላኛው የአርሲ ነገሌ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ አሠልጣኝ ሲሳይ በቀለም መሰል ሥልጠናዎች በስፋት ሊሰጡ እንደሚገባ አመላክቷል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪና ኤሌክትሮ ቴክኖሎጂ የኢንዱስትሪ የተግባር ልምድ ለወሰዱ አሰልጣኝ መምህራንና ለፕሮጀክቱ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት እውቅና ሰጥቷል።