በክልሉ ለተጀመሩ የልማት ስራዎች ስኬታማነት ሌብነትንና ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል የክልሉ ነዋሪዎች ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል

ጋምቤላ ፤ ህዳር 21/2016 (ኢዜአ) ፡-   በጋምቤላ ክልል ለተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ስኬታማነት ሌብነትንና ብልሹ አሰራሮችን በመታገል ረገድ የሁሉም የክልሉ ነዋሪ ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ ተመለከተ።

‘‘ሙስና የጋራ ጠላታችን ነው ፤በህብረት እንታገል’’ በሚል መሪ ሃሳብ የዓለም የፀረ- ሙስና ቀን በክልል ደረጃ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ተወካይና የፀረ- ሙስና ግብረ ሃይል ጸሃፊ አቶ ብረሃኑ ደጀኔ፣ በፓናል ውይይቱ ላይ እንዳሉት ሙስና የሀገርን ልማትና እድገት የሚገታ ችግር ነው ።

ሙስናና ብልሹ አሰራሮች የሀገርን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴን የሚያናጋና ዜጎችን ለእንግልትና ለከፋ ድህነት የሚዳርግ አደገኛ ወንጀል መሆኑን ተናግረዋል።

የሙስናና ብልሹ አሰራሮችን በሚፈለገው ልክ መግታት ካልተቻለ የህዝቡን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ እንደማያስችል ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም በጋምቤላ ክልል ሌብነትና ብልሹ አሰራርን በመታገል የታለመውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ግብ መሳካት ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲያበረክት  ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ ስነ-ምግባርና ፀረ- ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳይመን ቱሪያል በበኩላቸው የሙስና ትግሉ ፍሬያማ ሊሆን የሚችለው የሁሉም ዜጋ ተሳትፎና ትብብር መጠናከር ሲችል መሆኑን ገልጸዋል። 

ስለሆነም በኮሚሽኑ እየተካሄዱ ለሚገኙት የፀረ-በሙስና ትግል መሳካት ህዝቡ የተቻለውን ሁሉ ድጋፍና ትብብር እንዲያደረግላቸው ጠይቀዋል።

በተለይም የትምህርት ማስረጃዎች እንደ ክልል የማጣራት ስራ መጀመሩን ጠቁመዋል። 

በግንባታ ዘርፍና  የተመዘበሩ ገንዘቦችን ለማስመለስ በተቋሙ ግብረ ኃይሉ በኩል እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ኮንግ ጆክ በሰጡት አስተያየት ኮሚሽኑ የሚመዘበሩ የመንግስትና የህዝብ ሃብትን በማስመለስ ረገድ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

ኮሚሽኑ በግንባታና በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች በኩል የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን በማጥራት ረገድ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ የጠየቁት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ደሳለኝ ብሩ ናቸው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም