በጌዴኦ ዞን በተያዘው ዓመት ከ40 ሚሊዮን በላይ የእንሰት ችግኝ ይተከላል

 ዲላ ፤ ህዳር 21/2016 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጌዴኦ ዞን በተያዘው ዓመት ከ40 ሚሊዮን በላይ የእንሰት ችግኞችን ለመትከል የዘር ብዜት ስራ መጀመሩን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ።

የብዜት ስራው በዞኑ ኮቾሬ ወረዳ ዛሬ በይፋ የተጀመረ ሲሆን በቀጣይ መጋቢትና ሚያዚያ ወራት ለተከላ የሚሆኑ ችግኞችን ለማዘጋጀት የዘር ብዜት ሥራው የሚረዳ መሆኑም ተገልጿል።

የዞኑ ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ታጠቅ ዶሪ በወቅቱ እንዳሉት፤ በዞኑ የእንሰት ልማትን በማስፋት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ዞኑን የእንሰት ችግኝ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው።

በተለይ የእንሰት ልማት ስራን በቴክኖሎጂ በማገዝ ምርታማነትን ለማሳደግ እየታዩ ያሉ ጅምር ጥረቶችን ለማጠናከር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም በተያዘው ዓመት ከ40 ሚሊዮን በላይ የእንሰት ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን ጠቅሰው ባለፉት ሁለት አመታት ለ"አንድ አርሶ አደር መቶ የእንሰት ችግኝ" በሚል ሃሳብ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል። 

በተያዘውም አመት በእንሰት ልማት የተጀመሩ ጥረቶች እንዲሳኩ አርሶ አደሮችና ባለድርሻ አካላት በነቂስ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

በወረዳው አርሶ አደሩ እንሰትን በስፋት እንዲያለማ በማድረግ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥም በተጨማሪ ገቢ እያገኘ ነው ያሉት ደግሞ የራጴ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታምራት ዴልቦ ናቸው። 

በወረዳው አሁን ላይ የተጀመረው የእንሰት ሰብል ስራ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየታዩበት እንደሆነ ጠቅሰው በተያዘው አመት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

የራጴ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አማኑኤል ወርቁ በበኩላቸው እንሰት ከምግብነት በተጨማሪም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

በወረዳው እንሰትን በተናጠልና በስብጥር  በማልማት የአርሶ አደሩን ገቢ ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰው በተያዘው ዓመትም ከ2 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል የዘር ብዜት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

እንሰት የግብርና ልማት ስራች መሰረት ነው ያሉት ደግሞ የወረዳው አርሶ አደር ይጨነቁ ቦጋለ ናቸው።

ምርቱ ከምግብ ዋስትና ባለፈ ለአፈር ለምነት፣ ለተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት እንዲሁም ተረፈ ምርቱን ለገበያ በማቅረብ እየተጠቀሙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በተያዘውም ዓመት ከ1 ሺህ በላይ እንሰት ለመትከል ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም የዘር ብዜት ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም