በዓሉ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን በአንድ ጥላ በማሰባሰብ ባህልና እሴቶቻቸው ጎልቶ እንዲወጣ አድርጓል-የሰመራ ሎጊያ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በዓሉ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን በአንድ ጥላ በማሰባሰብ ባህልና እሴቶቻቸው ጎልቶ እንዲወጣ አድርጓል-የሰመራ ሎጊያ ከተማ ነዋሪዎች

ሰመራ፤ ህዳር 21/2016 (ኢዜአ)፦በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን በአንድ ጥላ ስር ከማሰባሰብ ባለፈ ባህልና እሴቶቻቸው ጎልቶ እንዲወጣ ያደረገ ነው ሲሉ በአፋር ክልል የሰመራ ሎጊያ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
በዓሉ እርስ በርስ ለመተዋወቅ፣ አንድነትን ለማጠናከር እና እኩልነትን በተግባር ለማረጋገጥ የቻሉበት መሆኑንም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
18ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በአፋር ከልል ደረጃ ሲከበር የተሳተፉ የከተማው ነዋሪዎች እንዳሉት፣ ባለፉት ዓመታት የተከበረው በዓል የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እርስ በርስ እንዲተዋወቁ አድርጓል።
አንዱ የሌላውን ባህል እንዲያውቅና እንዲያከብር እንዲሁም ተደብቀው የነበሩ ቱባ ባህሎች አደባባይ እንዲወጡ ማድረጉን ገልጸዋል።
በተጨማሪም እኩልነትን በተግባር ከማሳየት ባለፈ፤ የአገር ባለቤትነት ስሜት በብሔር ብሔረሰቦች መካከል መሠረት እንዲይዝ እያደረገ መሆኑን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የሠመራ ሎጊያ ከተማ ነዋሪ አቶ ኑሩ ደበሌ በየዓመቱ በሚከበረው በዓል ላይ እንደሚሳተፉ ገልጸው፣ በዓሉ የእርስ በርስ ትብብርን ለማጠናከር ይገኛል ብለዋል።
''ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ ተያይዘን ለአገር ልማት በአብሮነት መጓዝ ይገባናል'' ያሉት አቶ ኑሩ፣ በዓሉ ብሔር ብሔረሰቦች በአንድ ጥላ አንዲሰባሰቡ አስችሏል ብለዋል።
የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ባህልና እሴቶች ቀደም ባሉ ሥርአቶች ተገቢ ትኩረት ሳይሰጣቸው መቆየታቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ ሰይድ ሙክተባ የተባሉ የከተማው ነዋሪ ናቸው።
ቀኑ መከበሩ ህዝቦች ባህልና አሴታቸውን እንዲያጎለብቱ፣ እኩልነትን በተግባር እንዲያረጋግጡና አብሮነትን እንዲያጠናክሩ አስችሏል ሲሉም ገልጸዋል።
የማይታወቁ ብሔረሰቦች ባህልና ቋንቋቸው እንዲታወቅ ማድረጉንም ጠቁመዋል።
የብሔር ብሔረሰቦችን ቱባ ባህል፣ ቋንቋና እሴቶች ለማጎልበት በዓሉ ዓይነተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የገለጹት ደግሞ አቶ ሁሴን መሐመድ የተባሉ የከተማው ነዋሪ ናቸው።
እንደ እሳቸው ገለጻ በዓሉ በየዓመቱ መከበሩ አንዱ ብሔር ከሌላው ጋር እንዲተዋወቅ፣ ተከባብሮ አንዲኖርና በአገራዊ ጉዳይ አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ እያደረገ ነው።
የሠመራ ከተማ ነዋሪ ወጣት አሊ ሰለለ በበኩሉ በዓሉ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአብሮነት ደምቀው የሚታዩበት መሆኑን ገልጿል።
በበዓሉ ብሔር/ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቋንቋቸውን፣ ማንነታቸው እና ቱባ ባህላቸውን በአብሮነት ሲያሳዩ የኢትዮጵያዊያን የተለያዩ መልኮች ይንጸባረቃሉ ያለው ወጣት አሊ፣ በዓሉ አብሮነትን ስለሚያጎለብት መጠናከር አለበት ብሏል።
ዘንድሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ለ18ኛ ጊዜ የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ህዳር 29 ቀን 2016 ዓ.ም "ብዝሃነትና እኩልነት ለአገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚከበር ታውቋል።