ምክር ቤቱ የአበባ አልሚ ድርጅቶች የኬሚካል አያያዝና አወጋገድ እንዲስተካከል አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ የአበባ አልሚ ድርጅቶች የኬሚካል አያያዝና አወጋገድ እንዲስተካከል አሳሰበ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 21/2016 (ኢዜአ) ፡-በአበባ አልሚ ድርጅቶች የሚታየውን የኬሚካል አያያዝና አወጋገድ ክፍተት እንዲስተካከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በግብርና ሚኒስቴር የአበባ እርሻ ልማት ምርታማነትና የአካባቢ አያያዝ ስርዓት ውጤታማነት የ2014/15 የክዋኔ ኦዲት ላይ ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ሀራሬ ሞሲሳ እንዳሉት የግብርና ሚኒስቴር የአበባ ልማት በሚካሄድባቸው ስፍራዎች የአካባቢ ብክለት መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ ሊሰራ ይገባል።
ለአበባ እርሻ ጥቅም ላይ የሚውሉ ኬሚካሎች የአያያዝ እና የአወጋገድ ክፍተት የሚያደርስውን ተዕጽኖ ለመፍታት በጥናት የተመሰረተ ምላሽ መስጠት እንደሚገባውም ነው የተናገሩት።
በተለይ በአካባቢዎቹ ብክለትን ለመቀነስ የተጀመሩ ስራዎች በተጠናከረ ሁኔታ ሊተገበሩ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በክዋኔ ሪፖርት ግኝት ላይ ከአበባ ልማት እርሻዎች የሚወጣ ኬሚካል በሰውና በእንስሳት ጤና ላይ ጉዳት ማድረሱ የተገለጸ በመሆኑ ይህን ችግር ለመፍታት በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው የክዋኔ ኦዲቱን ለማስተካከል የተደረገው ጥረት አበረታች መሆኑን አንስተው በዘርፉ የህግ-ማዕቀፍ በማውጣት ሊተገበር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከአበባ እርሻ የሚለቀቁ ኬሚካሎች በትክክል እያደረሱ ያለውን ጉዳት ማጣራት እና በአካባቢው ካሉ አርሶ አደሮችን ጋር በቅርበት መስራት ይገባል ሲሉ አክለዋል።
በቀጣይ ለእርሻው የኢንቨስትመንት ፍቃድ ሲሰጥ ከውሃ አካላት አካባቢዎች ራቅ ያሉ ቢሆኑ ተመራጭ መሆኑን አንስተዋል።
በሰራተኛ የስራ ደህንነት ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባም ገልጸው፤ ምርቱ በሚመረትበት ቦታ ላይ ከስር የፕላስቲክ ንጣፍ በሁሉም ፋብሪካዎች ላይ ሊደረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መለስ መኮንን እንዳሉት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የግብርናና የገጠር ልማት ማሻሻያ ፖሊሲ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግና ተግዳሮቶችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም ገልጸዋል።
አሁን ምርት ላይ ከሚገኙት 63 ፋብሪካዎች ውስጥ 41 የሚሆኑት ላይ የፍሳሽ አወጋገድን ለማጣራት የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን አክለዋል።
ለግብርናው ዘርፍ የሚገቡ ኬሚካሎች የተመዘገቡ እና ቁጥጥር የሚደረግባቸው መሆኑን አስታውሰዋል።
ወደ አገር ውስጥ ከገቡም በኋላ በአግባቡ እንዲወገዱ መመሪያ መኖሩን ገልጸው፤ መመሪያው መተግበሩን በመከታተል ችግሩን ለማስወገድ ጥረት እናደርጋለን ብለዋል።