የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ መፍትሄዎች 30 ቢሊየን ዶላር ለመስጠት ቃል ገባች - ኢዜአ አማርኛ
የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ መፍትሄዎች 30 ቢሊየን ዶላር ለመስጠት ቃል ገባች

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 21/2016 (ኢዜአ)፡- የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ መፍትሄዎች ለሚደረገው ጥረት 30 ቢሊየን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብታለች።
የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች ፕሬዝዳንት ሼህ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናሕያን የኮፕ 28 ጉባኤን በከፈቱበት ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመዋጋትና ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ሀገራቸው 30 ቢሊየን ዶላር እንደምትለግስ ቃል ገብተዋል።
ገንዘቡ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት የሚያጋጥመውን የፋይናንስ ክፍተት ለመሙላትና ለማጠናከር እንደሚውል ተናግረዋል።
ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ በንጹህ ሃይል ዘርፍ ላይ መዋዕለ-ነዋይን ለማፍሰስና የንጹህ ሃይል ሽግግር ለማድረግ በቂ የሆነ የፋይናንስ አቅርቦት እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል።
ኮፕ28 ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ መፍትሄዎች ሀገራት እንዲተባበሩ፣ አንዲወያዩና ውሳኔዎችን እንዲያሳልፉ በማሰብ የተዘጋጀ ጉባኤ ነው ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖዎችን ለመዋጋት የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች በርካታ ስራዎችን መስራቷን ጠቅሰው፤ በተለይ የካርበን ልቀት መጠንን እ.አ.አ በ2030 በ40 በመቶ ለመቀነስና በ2050 ደግሞ ዜሮ ለማድረስ የተደረሰውን ስምምነት ለማሳካት በንጹህ ሃይል ዘርፍ ላይ መዋዕለ ነዋይ እያፈሰሰች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዓመታዊ የአየር ንብረት ጉባኤ በዱባይ እየተካሄደ ሲሆን የሀገራት መሪዎች የአየር ንብረት ለውጥ በተለይ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ላይ እያደረሰ የሚገኘውን ተጽእኖ ለመዋጋት የሚጠበቅባቸውን ፈንድ ለመመደብ ቃል ይገባሉ ትብሎ ይጠበቃል።