በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት የሰው ልጆች ህልውና አደጋ ላይ ናቸው- ተመድ - ኢዜአ አማርኛ
በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት የሰው ልጆች ህልውና አደጋ ላይ ናቸው- ተመድ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 21/2016 (ኢዜአ)፦ የአየር ንብረት መዛባት በሰው ልጆች ህልውና ላይ አደጋ የደቀነ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስገነዘበ።
የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ዱባይ እየተካሄደ ባለው ኮፕ 28 የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር አሁን ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ለሰው ልጆች ህልውና አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።
በዱባይ እየተደረገ ባለው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የሃገራት መሪዎች ችግሩን ለመከላከል የሚያስችል ተግባራዊና ተስፋ ሰጪ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ዋና ጸሃፊው ጥሪ አቅርበዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል የተሻለ ዓለም ለመፍጠር “በአመራር ብቃት፣ በአለምአቀፍ ትብብር እና በፖለቲካ ቁርጠኝነት ተግባራዊ እርምጃ እንውሰድ” ሲሉ ጥሪ ያቀረቡት ዋና ጸሃፊው፤ ከአመታት በፊት መከናወን የነበረባቸው በርካታ ውዝፍ ስራዎች አሉ ብለዋል።
በማደግ ላይ ያሉ ሃገራት ባልፈጠሩት ችግር ጉዳት እያስተናገዱ እንደሆነ የገለጹት ጉቴሬዝ፤ የበለጸጉ አገራት ቀደም ሲል ቃል የገቡትን የፋይናንስ ድጋፍ ተግባራዊ እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል።
ድርጅቱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2030 የታዳሽ ሃይል አጠቃቀም በሶስት እጥፍ እንዲያድግ ፍላጎት እንዳለው የተገለጸ ሲሆን ከተፈጥሮ ሃብት ከባቢ ጋር የሚስማሙት የንፋስ፣ የጸሃይ፣ የእንፋሎትና የውሃ ሃይል ምንጮች እንዲስፋፉ እያበረታታ መሆኑንም አሳውቋል።
ድርጅቱ የአየር ንብረት መለወጥን ታሳቢ ያደረጉ ስራዎች ለመተግበር የገንዘብ ምንጮች እንዲገኙ አፋጣኝ እርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚገባ ማሳሰቡን የአናዶሉ ዘግቧል።