የተቋማት ትኩረትና ቅንጅታዊ አሰራር ማነስ የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ላይ ጫና እያሳደረ ነው - የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ፤ ህዳር 21/2016 (ኢዜአ) ፦የተቋማት ትኩረትና ቅንጅታዊ አሰራር ማነስ የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ መሆኑን የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ገለጸ። 

ብሄራዊ የብዝሃ ሕይወት ስትራቴጂና የድርጊት መርሃ-ግብር ብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ የድህረ 2020 የብዝሃ ሕይወት ማዕቀፍ በተመለከተ ውይይት አካሂዷል።   

የድህረ 2020 የብዝሃ ሕይወት ማዕቀፍ ከሕዳር 28 እስከ ታህሳስ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በካናዳ ሞንትሪያል በተካሄደው 15ኛው ዓለም አቀፍ የብዝሃ ሕይወት ጉባኤ ላይ የብዝሃ ሕይወት ሥምምነት አገራት በጋራ እንዲተገብሩት ታስቦ የጸደቀ ዓለም አቀፍ ማዕቀፍ ነው።   

የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማርዮ ኢትዮጵያ ከድህረ 2020 የብዝሃ ሕይወት ማዕቀፍ ጋር የሚጣጣም ብሄራዊ የብዝሃ ሕይወት ስትራቴጄና የድርጊት መርሃ-ግብር ለመቅረጽ የዝግጅት ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ ተናግረዋል።   

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የብዝሃ ሕይወት ሃብት ካላቸው 20 ቀዳሚ አገራት አንዷ መሆኗን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ ይህንን ትልቅ ሃብት ለመጠበቅ የበርካታ አካላት ቅንጅታዊ ስራ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።  

ይሁን እንጂ በተቋማት ላይ የሚስተዋለው የትኩረትና ተባብሮ የመስራት ውስንነት የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ ነው ብለዋል።  

ለአብነትም የኢንቨስትመንት፣ የኢንዱስትሪ ልማት፣ የመንገድና መሰል መሰረተ ልማቶች የግንባታ ፈቃድ ከመሰጠቱና ወደ ትግበራ ከመገባቱ አስቀድሞ ከብዝሃ ሕይወት አኳያ የሚኖረውን አሉታዊ ተጽእኖ በአግባቡ ከማጥናትና ውሳኔ ከመስጠት አኳያ ጉድለቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።   

በዚህም የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ጥበቃ የሚፈለገውን ያክል ውጤት አለማስመዝገቡን ገልጸዋል።

በመሆኑም ተቋማት የሚስሯቸው ሥራዎች የብዝሃ ሕይወት ጥበቃን ከግምት ያስገቡ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።   

ተቋማቱ የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ዘለቄታዊ አጠቃቀምን የዕቅዳቸው አካል አድርገው በትኩረት መስራት አለባቸው ብለዋል።  

ብዝሃ ሕይወትን ከመጠበቅ አኳያ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የአረንጓዴ አሻራ፣ የገበታ ለሸገር፣ ለሀገርና ለትውልድ ፕሮጀክቶች በተምሳሌትነት የሚነሱ ናቸው ብለዋል።   

ተቋማትም ይህንን ተሞክሮ በማስፋት ለብዝሃ ሕይወት ጥበቃ በጎ አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈለቀ ወልደየስ በበኩላቸው ፖሊሲዎችና ዕቅዶች ሲወጡ ለብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ምላሽ መስጠትን ከግምት ውስጥ ሊያስገቡ እንደሚገባ ተናግረዋል።


 

በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች የብዝሃ ሕይወት ሃብት ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ጠቅሰው ኢንስቲትዩቱ በተቻለው መጠን ብዝሃ ሕይወትን ከጉዳት ለመታደግ እየሰራ ነው ብለዋል።   

በዚህም የብዝሃ ሕይወት ሀብት የማንበር፣ ዘለቄታ ያለው አጠቃቀም የማረጋጥና ከሀብቱ የሚገኘውን ጥቅም በፍትሃዊነት ማጋራት የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።   

የድህረ 2020 የብዝሃ ሕይወት ማዕቀፍ የዝግጅት ትግበራ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር ምስክር ተሰማ የብዝሃ ሕይወት ጥፋት ከአየር ንብረት ለውጥና  ብክለት ባልተናነሰ ዓለምን እየፈተነ መሆኑን ገልጸዋል።   


 

ለዚህም እ.አ.አ እስከ 2030 የሚተገበር አካታችና አሳታፊ የብዝሃ ሕይወት ስትራቴጂና የድርጊት መርሃ-ግብር ለማዘጋጀት ዕቅድ ተይዞ በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።  

ከዝግጅት እስከ ትግበራ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚና ወሳኝ በመሆኑ በተለይ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ተቋማት የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ የትውልድ ጉዳይ መሆኑን ተረድተው ለፕሮጀክቱ ስኬት መረባረብ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።  

በዚሁ ረገድ ከ29 በላይ ተቋማትን በአባልነት የያዘው የብዝሃ ሕይወት ስትራቴጂና የድርጊት መርሃ-ግብር  ብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ሚናም የላቀ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም