ጽዳትን ባህሉ ያደረገ ትውልድ ለመገንባት ትምህርት ቤቶች ላይ በጋራ መስራት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ጽዳትን ባህሉ ያደረገ ትውልድ ለመገንባት ትምህርት ቤቶች ላይ በጋራ መስራት ይገባል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 21/2016 (ኢዜአ) ፦ጽዳትን ባህሉ ያደረገ ትውልድ ለመገንባት ትምህርት ቤቶች ላይ በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ።
ኤጀንሲው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ጋር በመሆን የ2016 ዓ.ም የትምህርት ቤቶች የጽዳት ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር አካሒዷል፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር እሸቱ ለማ በማስጀመሪያ መርሃ-ግብሩ ላይ እንዳሉት፣ በ2014 ዓ.ም ጽዳትን በተመለከተ ከትምህርት ቢሮ ጋር በጋራ ለመስራት ስምምነት መደረጉን አስታውሰዋል።
በስምምነቱ መሰረትም በየዓመቱ የትምህርት ቤቶች ንቅናቄ በማድረግ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ላይ የጽዳት ስራ በስፋት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
በዚህም የትምህርት ቤቶችን አካባቢ ጽዳት ከመጠበቅ ባሻገር ተማሪዎች ጽዳትን በተመለከተ ግንዛቤያቸው እንዲያድግ የሚያስችሉ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አመልክተዋል፡፡
በዚህም በርካታ ሞዴል ትምህርት ቤቶችን መፍጠር መቻሉን የጠቆሙት ዶክተር እሽቱ፣ ከነዚህ መካከል እቴጌ መነን የልጃገረዶች አዳሪ ትምህርት ቤት አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ቆሻሻን ከመጸየፍ ባሻገር አካባቢውን የሚያጸዳ ትውልድ ለማፍራት ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው የጽዳት ልምምድ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ የጽዳት ስራን ባህሉ ያደረገ ትውልድ ለመገንባት ትምህርት ቤቶች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ ታጋይቱ አባቡ በበኩላቸው፣ ባለፉት ዓመታት በትምህርት ቤቶች ላይ በተደረገ የጽዳት ዘመቻ በርካታ ሞዴል ትምህርት ቤቶችን መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በርካታ ትምህርት ቤቶችን ጽዱ፣ ውብና ማራኪ በማድረግ ለመማር ማስተማር ስራው ምቹ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
ሃላፊዎቹ በትምህርት ቤቶች ላይ የሚደረገው የጽዳት ንቅናቄ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
የማስጀመሪያ መርሃ-ግብሩ የተካሔደው እቴጌ መነን የልጃገረዶች አዳሪ ትምህርት ቤት ሲሆን የኤጀንሲውን ዋና ዳይሬክተር ጨምሮ ፣ የትምህርት ቢሮና የጉለሌ ክፍለ ከተማ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡