በክልሉ ለሌብነት ተጋላጭ የሆኑ አሰራሮችን በማሻሻል የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ የተቀናጀ ጥረት ይደረጋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ለሌብነት ተጋላጭ የሆኑ አሰራሮችን በማሻሻል የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ የተቀናጀ ጥረት ይደረጋል

ዲላ፤ ህዳር 21/2016 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለሌብነትና ብልሹ አሰራር የተጋለጡ አሰራሮችን በማሻሻል የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ የተቀናጀ ጥረት እንደሚደረግ የክልሉ መንግስት ገለጸ።
በክልሉ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ ከተንዛዛ ቢሮክራሲያዊ አሰራር ነጻ የሆነ የመሬት አቅርቦት መዘጋጀቱም ተመላክቷል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ አለማየሁ ባውዲ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ በክልል ምስረታው ለስራ የሚያግዝ ምክረ ሃሳብና የፋይናንስ ድጋፍ አግኝተናል።
ይህም አሁን በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተሰጠ የሚገኘው የአመራር ስልጠና ክልሉ ከጅምሩ ወቅቱን የዋጀና ለስራ የተነሳሳ የአመራር ስብስብና በቂ እገዛ እንዲያገኝ ማድረጉን አስረድተዋል።
ክልሉ የኦሞ ወንዝን ጨምሮ በርካታ ጅረቶችና ተፋሰሶች የሚያልፉበት ለግብርና ልማት ምቹ የሆነ ልቅ መሬትና ውሃ ባለቤት መሆኑን ጠቅሰዋል።
መልካም አጋጣሚዎችን ከክልሉ ጸጋዎች ጋር በማቀናጀት ለቀጣይ አመታት መሰረት የሚጥል የግብርና ልማትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ በቡና፣ በመስኖ ልማት፣ በቅባትና በቅመማ ቅመም ሰብሎች ክልሉ ያለውን እምቅ አቅም አውጥቶ በመጠቀም የውጭ የግብርና ምርት አቅርቦትን ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አመላክተዋል።
በክልሉ በመሬት አቅርቦት በአገልግሎት አሰጣጥና በመሰል ዘርፎች ላይ ያሉ ግልፅነት የጎደላቸው አሰራሮች እንደነበሩ አቶ አለማየሁ ባውዲ አንስተዋል።
ይህም የክልሉን ዕድገት ከጅምሩ የሚያቀጭጭ መሆኑን ጠቅሰው ለሌብነትና ብልሹ አሰራር የተጋለጡ አሰራሮችን በማሻሻል ያደረ የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
በተለይ በሌብነት ላይ የተሳተፉ አመራሮች ላይ እርምጃ ከመውሰድ በዘለለ ማህበረሰቡን ያሳተፈ የጸረ ሙስና ትግል እየተካሄደ መሆኑንም አስረድተዋል።
በክልሉ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማጠናከር ምርታማነትን ለማሳደግና የስራ አጥነትን ችግር ለመቅረፍ ትኩረት መደረጉንም ተናግረዋል።
ለዚህም ከተንዛዛ ቢሮክራሲያዊ አሰራር ነፃ የሆነ የመሬት አቅርቦት መዘጋጀቱን ጠቅሰው የግል ባለ ሃብቱም እድሉን እንዲጠቀም ጥሪ አቅርበዋል።
በክልሉ የተወጠኑ እቅዶችን ከግብ ለማድረስ ጊዜና የተናበበ ጥረት እንደሚጠይቅ ያነሱት የመንግስት ተጠሪው የክልሉ ህዝቦች ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ተሳትፎአቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በተለይ የክልሉን ብዝሃነት እንደ እዳ ሊጠቀሙ የሚፈልጉ አካላትን በመከላከል ገቢን በማሳደግ ወጪን በውስጥ አቅም ለመሸፈን የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙም ጠይቀዋል።