የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ማኀበር መመስረት ለብሔራዊ ጥቅም መከበር የጎላ ጠቀሜታ አለው - አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ማኀበር መመስረት ለብሔራዊ ጥቅም መከበር የጎላ ጠቀሜታ አለው - አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 21/2016 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ማኀበር መመስረት ለብሔራዊ ጥቅም መከበር የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያየ ጊዜ አገራቸውን ለረጅም ጊዜ በልዩ ልዩ ኃላፊነቶች ሲያገለግሉ የነበሩ የቀድሞ እና አንጋፋ አምባሳደሮችን፣ ዲፕሎማቶችንና በአሁኑ ወቅት እያገለገሉ ያሉ የመሥሪያ ቤቱ ባለሙያዎችን ያካተተ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ማኀበር ተመስርቷል።
በማኀበሩ ምስረታ ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የአገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም እና ክብር እንዲጠበቅ ያደረጉ አንጋፋ ዲፕሎማቶችን እና የአሁኑን ትውልድ ባለሙያዎች የሚያሰባስበው ማኀበር መመስረቱ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።
ማኀበሩ በውጭ ግንኙነት ሥራ ውስጥ በጥናት እና ምርምር፣ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን በማሳየት እንዲሁም ወጣቶችን በማሰልጠን የእውቀት ሽግግር በማድረግ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ አምባሳደሩ መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በማኀበሩ ምሥረታ ላይ የተገኙ አንጋፋ ዲፕሎማቶች የሙያ ማኀበር መመስረቱ የዲፕሎማሲ ሙያ እና ጥበብ እንዲጎለብት እና በባለሙያዎች መካከል ማኀበራዊ ትስስር እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ማኀበር መመስረቱ በተደራጀ መልኩ ሙያዊ አስተዋጽኦ ለማድረግ እና የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ እንደሚያስችልም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ማኀበር ጠቅላላ ጉባኤ ማህበሩን የሚመሩ አመራሮችን በመምረጥም መጠናቀቁ ተገልጿል።