የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበር ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከር ወሳኝ ድርሻ አለው - ኢዜአ አማርኛ
የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበር ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከር ወሳኝ ድርሻ አለው

ሚዛን አማን/ዲላ ፤ ህዳር 21/2016 (ኢዜአ) ፦ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበሩ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን እያጠናከረ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአስተዳደር አካላትና ነዋሪዎች ገለጹ።
''ብዝሃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት!''በሚል መሪ ቃል 18ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በቴፒና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዲላ ከተሞች ተከብሯል።
በቴፒ በተከበረው በዓል ላይ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ወንድሙ ኩርታ እንደተናገሩት፤ የክልሉ ብሔረሰቦችን አንድነት በማጠናከር ኅብረ ብሔራዊነትን ለማጽናት እየተሰራ ነው።
በክልሉ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን በማጠናከር፣ ልዩነታችንን ለአንድነታችን ውበት አድርጎ የመጠቀም ልምድ አጎልብተን የሰላም ተምሳሌት ለመሆን ይሰራል ብለዋል።
በጌዴኦ ዞን የኮቾሬ ወረዳ ነዋሪዋ ወይዘሮ መሠረት ታደሰ ቀኑ ''ባህላችንና እሴቶቻችንን በአደባባይ እንዲንጸባረቅ ከማስቻሉም በላይ፤ እርስ በርስ ለመተዋወቅና ብሎም ኅብረብሔራዊነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስተዋፅኦው ከፍተኛ ነው'' ሲሉ ተናግረዋል።
በዓሉ በልዩነት ውስጥ አንድነት እንዲጎለብት ያስቻለ ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዋ፣ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ለሁለንተናዊ እድገት በትጋት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ መቱ አኩ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ሥር እንዲሰድ የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት ማክበርና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማስከበር እንደሚገባ ተናግረዋል ።
ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ውስጥ ያለውን ውበትና አቅም በማስቀጠል ሁለንተናዊ ብልፅግና እንዲረጋገጥ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የገለጹት የይርጋጨፌ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ውቢት ናቸው።
የዲላ ከተማ ነዋሪው አቶ ተሾመ አናጋው ቀኑ ከእርስ በርስ ትውውቅ ባለፈ፤ የኢትዮጵያ ገፅታዎች በዓለም ለማስተዋወቅ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
በተለይ በብዝሃነት ውስጥ ያሉ ልዩነቶችን አቻችሎ በማስቀጠል የሀገር እንድነትን ለማጽናት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ በማመላከት።
በቴፒ በዓሉን ከታደሙት መካከል አቶ ግርማ ደፋር የብሔረሰቦች ዕኩልነትና የጋራ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
አቶ ሻንቆ ጋኪናንስ የተባሉ ሌላው የበዓሉ ተሳታፊ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ብዝኃነትን ያከበረ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ማጎልበት ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ወይዘሮ መሠረት በላይነህ በዓሉ የብሔር፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች አደባባይ ወጥተው እንዲተዋወቁ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ኅብረ-ብሔራዊነትን በማጠናከርና ሰላምን ማስጠበቅ ከሁሉም ይጠበቃል ያሉት ምክትል አፈ ጉባዔዋ፣ ማህበረሰቡ አንድነቱን አፅንቶ በማስቀጠል የልማት እንቅስቃሴውን እንዲያፋጥን አሳስበዋል።
የዘንድሮው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ኅዳር 29 ቀን 2016 በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ይከበራል።
ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ የአስተዳደር መዋቅሮችና ተቋማት በዓሉን በተያዘው ወር በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበሩት ይገኛሉ።