ከአፋር ክልል ለሀገራዊ ምክክር አጀንዳ የሚያሰባስቡ ተሳታፊዎች መረጣ ከነገ ጀምሮ ይካሄዳል--ኮሚሽኑ

ሰመራ ፤ ህዳር 21/2016 (ኢዜአ) ፦ከአፋር ክልል ለሀገራዊ ምክክር አጀንዳ የሚያሰባስቡ ተሳታፊዎች መረጣ ከነገ ጀምሮ እንደሚካሄድ የኢትየጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር አይሮሪት መሐመድ አስታወቁ።

ኮሚሽነር አይሮሪት ዛሬ በሰመራ ከተማ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት በክልሉ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ለሀገራዊ ምክክር አጀንዳ የሚያሰባስቡ ተወካዮች መረጣ ከኅዳር 22 ቀን 2016 ጀምሮ ይከናወናል።

መረጣው የሚካሄደው ኮሚሽኑ ለተባባሪ አካላት በሰጠው ሥልጠና የተለዩ ተሳታፊዎች ከየወረዳዎቹ ከመረጧቸው 4ሺህ 320 ተሳታፊዎች መካከል መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህም የክልሉን 48 ወረዳዎች የማህበረሰብ ክፍሎች የሚወክሉ  864 ተሳታፊዎች እንደሚመረጡ አስረድተዋል።

እንደ ኮሚሽነሯ ገለጻ በመረጣው ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ የጎሳ መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አርብቶ አደሮች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ተፈናቃዮችና መምህራን ይወከላሉ።

ኮሚሽኑ የአጀንዳ አሰባሳቢ ተወካዮች መረጣው አካታችነትን፣ ግልጽነትን፣ አሳታፊነትንና ተዓማኒነት ያገናዘበ እንዲሆን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የማህበረሰቡ ተወካዮች መረጣ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ በንቃት እንዲሳተፍ ያሳሰቡት ዶክተር አይሮሪት፣ በዚህም ለሀገራዊ ምክክር ስኬት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል።

ባለፈው ወር በክልሉ የተካሄደው የተሳታፊዎች ልየታ ክልሉ ላደረገው ትብብርና ተሳትፎ ኮሚሽነሯ አመስግነዋል። 

የኢትየጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባለፈው ወር በክልሉ የተሳታፊዎች ልየታ ያካሄደ ሲሆን፣ በሁሉም ወረዳዎች ለተሰማሩ ተባባሪ አካላትም የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠቱን ለማወቅ ተችሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም