ብዝሃነትን በእኩልነት የምታስተናግድና በሃሳብ የበላይነት የበለጸገች ሃገርን ለመውረስ እንፈልጋለን-የዲላ ከተማ ተማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ብዝሃነትን በእኩልነት የምታስተናግድና በሃሳብ የበላይነት የበለጸገች ሃገርን ለመውረስ እንፈልጋለን-የዲላ ከተማ ተማሪዎች
ዲላ፤ህዳር 19/2016 (ኢዜአ) ብዝሃነትንና የአመለካከት ልዩነቶችን በእኩልነት የምታስተናግድና በሃሳብ የበላይነት የበለጸገች ሃገር ለመውረስ እንሻለን ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዲላ ከተማ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተናገሩ።
ተማሪዎቹ 18ኛውን የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን በተለያዩ አልባሳት ደምቀው አክብረውታል።
ለኢዜአ አስተያየቷን የሰጠችው በዲላ ከተማ የዳማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ትዝታ ሰለሞን እንዳለችው፤ ተፈጥሯዊ ልዩነቶች የግጭትና የመለያየት ምንጭ ሊሆኑ አይገባም።
ኢትዮጵያ የራሳቸው ባህልና ወግ ያላቸው በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ መሆኗን ጠቅሳ፤ "ይህም የሚያስደስት ማንነት እንዲኖረን አድርጓል" ብላለች።
"ብዝሃነትን በእኩል በማስተናገድ፣ የአመለካከት ልዩነቶችን በመቀበል ረገድ እንደ አገር ውስንነቶች እንዳሉን የሚነሱ "ግጭቶችና አለመግባባቶች አብነት ናቸው" ብላለች ።
18ኛውን የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዕለትን በሚገልፅ አለባበስ ከጓደኞቿ ጋር ያገኘናት የዲላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህር ቤት ተማሪ ቤተልሄም ጋሻ በበኩሏ "ዕለቱ እርስ በእርሳችን እንድንተዋወቅና እንድንግባባ ከማድረግ ባለፈ ልዩ መልክ፣ ቀለምና ውበት አለው" ብላለች።
የብሔር ብሔረሰቦች ቀን የህዝቦችን አንድነት የበለጠ የሚያጠናክር እንደሆነ የገለፀው ተማሪ ግሩም ማስረሻ፤ በክልሉ የሚገኙ ያልታወቁ ዉብ ባህሎች ጎልተው እንዲወጡ አበርክቶ እንዳለው ጠቅሷል።
ብዝሃነትን በእኩል ደረጃ የበለጠ የሚያስተናግድና በሃሳብ የበላይነት እጅግ የበለጸገ ማህበረሰብ ተፈጥሮ ማየት የእርሱ ምኞት መሆኑን ነው የገለጸው።
ኢትዮጵያ "የብሔር ብሔረሰቦች ድምር ውጤት ናት" የምትለው ደግሞ የዲላ ዶን ቦስኮ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ቅድስት ያዕቆብ ናት።
''ቀኑ መከበሩ ልዩነቶችን እንድንረዳና እንድንቀበል በማድረግ የጋራ አቅማችንን እንድንጠቀም ያስችላል'' ብላለች።
ብዝሃነት ፀጋ መሆኑን ጠቅሳ፤ የአመለካከት ልዩነቶች በእኩልነት የምታስተናግድ አገር ለመውረስ እንደምትሻ ተናግራለች።
''ብዝሃነትና እኩልነት ለአገር እድገት '' በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ የሚገኘው 18ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ዛሬ ተከብሯል።