በአዲስ አበባ ከተማ የቦክስ ስፖርት ውድድርን ለማስፋት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 21/2016 (ኢዜአ) ፦ በአዲስ አበባ ከተማ የቦክስ ስፖርት ውድድር ለማስፋት በዘርፉ ስመ ጥር ስፖርተኞችን ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ  ገለፀ።

"አዲስ ቦክስ ውድድር" በሚል ስያሜ የቦክስ ስፖርት ውድድር ትናንት ምሽት ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ተከናውኗል ።


 

በሁለቱም ፆታዎች ከ54 እስከ 81 ኪሎ ግራም ውድድር ተካሂዷል።

በታዳጊዎች 54 ኪሎ ግራም ልዑልሰገድ ወንዱ አማኑኤል ታምራትን ሲረታ በአዋቂ ሴቶች 54 ኪሎ ግራም ሀገሪ እማኙ ሮማን አሰፋን አሸንፋለች።

በተመሳሳይ በአዋቂ ወንዶች 54 ኪሎ ግራም ፍትዊ ጥኡማይ ዳዊት በቀለን ማሸነፍ ችሏል።

በ57 ኪሎ ግራም የወንዶች ውድድር በዘንድሮው የኦሊምፒክ ማጣሪያ ከአፍሪካ ተወዳዳሪዎች ጋር ተፋልሞ ለአገሩ የብር ሜዳልያ ይዞ የተመለሰው ፍቅረ ማርያም ያደሳ ቢላል አስራርን አሸንፏል።

በ63 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም አዋቂ ወንዶች መስፍን ብሩና አብርሃም ዓለም ፍልሚያቸውን ያካሄዱ ሲሆን በመስፍን ብሩ አሸናፊነት መጠናቀቅ ችሏል።

የውድድሩ የመጨረሻ ምድብ በሆነውና ብርቱ ፉክክር የታየበት 81 ኪሎ አዋቂ ወንዶች ፍልሚያ ሰይፉ ከበደ ከናትናኤል ነዋይ ጋር ተፋልሞ ማሸነፍ ችሏል።

በየምድቡ አሸናፊ ለሆኑ ቦክሰኞች የ15ሺህ ብር ሽልማት ሲበረከትላቸው ለተጋጣሚዎች ደግሞ የ10ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ በላይ ደጀን በውድድሩ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር፤ ፤ እንደነዚህ ዓይነት ውድድሮች መዘጋጀታቸው ስፖርቱን እንደሚያነቃቃ ገልፀዋል። 

በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች አገርን ወክለው የሚወዳደሩ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እንደሚረዳም ተናግረዋል።

በከተማው የሚገኙ የስፖርት ማኅበራትን በመደገፍና ከባለድርሻ አካላት፣ ከባለሃብቶችና  ስፖርትን ከሚወዱ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት የቦክስ ውድድሮች በከተማ ደረጃ በስፋት እንደሚዘጋጁ ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት ኢንጂነር አስቻለው ኃይለማርያም በበኩላቸው የቦክስ ስፖርት እየተዳከመ መምጣቱን ገልፀዋል። 

ስለሆነም የቦክስ ስፖርት እንዲነቃቃና አገርን በኦሊምፒክ የውድድር መድረክ የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለማፍራት የቦክስ ውድድሮችን በስፋት ማከናወን እንደሚገባ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም