እንደ አገር በሴቶች ላይ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
እንደ አገር በሴቶች ላይ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው

አዳማ ፤ህዳር 21/2016 (ኢዜአ)፡-እንደ አገር በሴቶች ላይ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አስገነዘቡ።
''ፆታዊ ጥቃትን መቼም፣ የትም፣ በምንም ዝም አንልም'' በሚል መሪ ሀሳብ የነጭ ሪቫን ቀንና የፆታዊ ጥቃት ማስቆሚያ ንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ በአዳማ ተካሄዷል።
ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዚሁ ወቅት ፆታዊ ጥቃት በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚያሳድረው የስነ-ልቦና፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ለቀጣይ 16 ቀናት የሚካሄደው ንቅናቄ በየደረጃው ያሉ የባለድርሻ አካላት ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጡ ያግዛል ብለዋል።
በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በስራ ቦታ የሴቶችና እናቶችን ጫና ለመቀነስ የህፃናት ማቆያ መገንባት፣ ህይወታቸው እንዲሻሻል የገቢ ምንጭና ሌሎች ተጠቃሚነታቸውን የሚያሳድጉ ስራዎች ትኩረት ሊያገኙ እንደሚገባም ገልጸዋል።
''ችግሩን በቀላሉ ማየት የለብንም'' ያሉት ፕሬዚዳንቷ ሴቶች፣ ህፃናትና እናቶችን ከወደቁበት የማንሳትና ስነ-ልቦናቸውን የመገንባት ስራ ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝም አሳስበዋል።
የፆታዊ ጥቃትን ለማስቆም ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባና ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበው እንደ አገር በሴቶች ላይ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አክለዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው ፆታዊ ጥቃት በሴቶች ላይ የስነ-ልቦና ጫና ከማሳደር ባለፈ ለውስብስብ ችግሮች ይዳርጋቸዋል ብለዋል።
ችግሩን በመከላከል የጤና፣ የስነ-ልቦና ጉዳትን ጨምሮ የሚደርስባቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር መግታት ይገባል ነው ያሉት።
በሚኒስቴሩ አስተባባሪነት ተጎጂዎች ጥቆማ የሚሰጡበት አድራሻ፣ የህግ፣ የምርመራና የህክምና፣ ጊዜያዊ ማረፊያና ማገገሚያ እንዲሁም የስነ-ልቦናና የመልሶ ማቋቋም ስራ በስፋት መሰራቱን አንስተዋል።
ሴቶችና ህፃናትን ከማንኛውም ፆታዊ ጥቃት ለመከላከል ሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተደድር አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በትብብር መስራት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።
ከመረጃ እጥረትና ከህግ ክፍተት አኳያ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ጠቅሰው ችግሮቹን ለመቅረፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቀጣይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ መብራት ባጫ ''ቀኑን ከማሰብ ባለፈ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለመዋጋት ቃላችንን የምናድስበት ነው'' ብለዋል።
የክልሉ መንግስት ሴቶችን በሁሉም መስኩ ለመደገፍ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም ሴቶች የመኖሪያ ቤት፣ የብድርና ቁጠባ አገልግሎት እንዲያገኙ እንዲሁም ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎቸው እንዲጠናከር እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።
በሴቶች ላይ የሚደርስ ፆታዊ ጥቃትን ማስቆምና ሴቶች በማህበራዊና ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማስቻል ስራ በአዳማ ከተማ ትልቅ ትኩረት ማግኘቱን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ ተናግረዋል።
በዚህም በከተማዋ ባለፈው ዓመት ከተገነቡ 500 መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ ለሴቶችና እናቶች መሰጠቱን ገልጸዋል።
ምንም ገቢ የሌላቸው ሴቶች የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸውና ሰርተው ራሳቸውን መለወጥ እንዲችሉ የከተማዋን ባለሃብቶች በማስተባበር ስራዎች መሰራታቸውንም ጠቅሰዋል።
በተመሳሳይ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ ከተማዋ ካላት 19 ወረዳዎች ውስጥ የሁለቱ ወረዳዎች የካቢኔ አባላት ሙሉ በሙሉ ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።