ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነት እንዲጨምር ቻይና ድጋፏን አጠናክራ ትቀጥላለች 

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 21/2016 (ኢዜአ)፦ ቻይና በኢትዮጵያ የግብርና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር  ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል በቻይና የብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ የግብርናና ገጠር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ተናገሩ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ ከቻይና ኮንግረስ ፓርቲ የግብርናና የገጠር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ተወያይተዋል።

በዚሁ ጊዜ የሁለቱ አገራት ስትራቴጂካዊ አጋርነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ መምጣቱ ተገልጿል።

ቻይና በኢትዮጵያ በመሰረተ ልማት፣ ግብርና፣ ትምህርትና ጤናን ጨምሮ በሁሉም መስኮች የምታደርጋቸው ድጋፎች ተጠናክሮ መቀጠሉም ነው የተነሳው።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ በዚሁ ጊዜ  እንዳሉት፤  ቻይና በአለም አቀፍ መድረኮች ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም የምታሳየውን ድጋፍ አድንቀዋል።


 

አገሪቱ የኢትዮጵያ ቁልፍ የልማት አጋር በመሆን በሁሉም መስኮች የምታሳየው ትብብር የሁለቱን አገሮች ስትራቴጂካዊ  የልማት አጋርነት  የበለጠ የሚያሳድግ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከአረንጓዴ ልማት ጀምሮ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራች መሆኑንም ነው ምክትል አፈ-ጉባኤዋ ያብራሩት።

የግብርና ሜካናይዜሽን ዘዴን በመጠቀም፣ ግብርናውን በማዘመንና  የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ ቻይና ልምዷን ለኢትዮጵያ እንድታጋራም ጠይቀዋል።

የሁለቱ አገራት የህዝብ ለህዝብና የፓርላማ ለፓርላማ ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር የልምድ ልውውጥ መድረኮችን ማመቻቸት እንደሚገባም ነው ምክትል አፈ-ጉባኤዋ ያመለከቱት።

በቻይና ብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ የግብርናና የገጠር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዱ ጂሃኦ በበኩላቸው አገራቸው ግብርናውን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የወሰደቻቸውን እርምጃዎች አብራርተዋል።

ቻይና በክላስተር በማረስና የግብርና መካናይዜሽንን በመጠቀም ምርቶችን በብዛትና በጥራት እያመረተች ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ  ከጥቂት አመታት ወዲህ የግብርናውን ክፍለ-ኢኮኖሚ ለማሳደግ እያከናወነች ያለው ስራ የሚደነቅ መሆኑንም አንስተዋል።

በተለይም በተፈጥሮ ሃብትና አካባቢ ጥበቃ ላይ እያሳየችው ያለው ተሳትፎ ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉም ነው የተናገሩት።

ቻይና የኢትዮጵያን ግብርናን ለማዘመን የተለያዩ የቴክኖሎጂ ድጋፎችን የምታደርግ መሆኑንም ነው ያረጋገጡት።

የሁለቱን አገራት የፓርላማ ለፓርላማ ግንኙነት የበለጠ በማሳደግ የልማት አጋርነታቸውን እንዲያጠናክሩ የኢትዮጵያ ፓርላማ አባላት ወደ ቻይና ሄደው የግብርናውን ዘርፍ እንዲጎበኙ ዕድል ይመቻቻል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም