ቀጥታ፡

በዓሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲተዋወቁና አንድነታቸውን እንዲጠናክሩ እያስቻለ ነው

ሐረር፤ ኅዳር 21/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል መከበር ዜጎች እርስ በርስ እንዲተዋወቁና አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ ያስቻለ መሆኑን የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

"ብዝሃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት!" በሚል መሪ ሃሳብ የዘንድሮው 18ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ለኢዜአ እንደገለጹት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል መከበር ዜጎች እርስ በርስ ከመታዋወቅ ባለፈ አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ አስችሏል።

የዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል `ሃላፊና የታሪክ ተመራማሪ ዶክተር ተማም ሐጂ አደም እንዳሉት በዓሉ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህሎቻቸውና እሴቶቻቸውን ለማስተዋወቅ እያስቻለ ነው።

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና የሕዝቦች አንድነትን ከማጠናከር ባለፈ እርስ በርስ እንዲደጋገፉና እንዲተሳሰቡ ማድረጉንም ተናግረዋል።

በዓሉ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተለያዩ ማንነቶች፣ ቱባ ባህሎች፣ ቋንቋና የአኗኗር ዘይቤ ጎልቶ እንዲወጣና ማስቻሉንም ዶክተር ተማም ጠቁመዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብቶች በእኩልነት እንዲከበር፣ ለአገር ሰላምና ልማት በጋራ እንዲሰሩ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ብለዋል።


 

በዩኒቨርሲቲው የታሪክ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶክተር መሐመድ ሀሰን በበኩላቸው በ1987 የጸደቀው የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በእኩልነት፣ በመቻቻልና በአብሮነት ለመኖር እንዳስቻላቸው አስረድተዋል።

በፌዴራላዊ ሥርዓት ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው ቋንቋቸውን፣ ባህሎቻቸውን፣ ማንነታቸውንና ሌሎች መገለጫዎቻቸውን እንዲያዳብሩ መንገድ ከፍቷል ሲሉም ገልጸዋል።

በዓሉ ዜጎች በጋራ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በንቃት በመሳተፍ ኅብረ ብሔራዊ የሆነች አገርን ለመገንባት መደላድል መፍጠሩንም ዶክተር መሐመድ አመልክተዋል።

ዶክተር መሐመድ እንዳሉት ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራላዊ ሥርዓቱ የራስን ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ቋንቋ፣ ባህል፣ ማንነትና ትውፊቶች እንድናውቅና እንድንጋራ አስተዋጽዎ አበርክቷል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ በዓሉን  በልማት ሥራዎች፣ በፓናል ውይይት እና በሌሎች መርሃ-ግብሮች አክብሯል።

በአገር አቀፍ ደረጃ የዘንድሮው 18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ኅዳር 29 ቀን 2016 ይከበራል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም