ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚያስችሉ ውይይቶች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተካሂደዋል - ኢዜአ አማርኛ
ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚያስችሉ ውይይቶች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተካሂደዋል

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 21/2016 (ኢዜአ) ፦ በሩብ ዓመቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚያስችሉና ምሁራንን በስፋት ያሳተፉ ውይይቶች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች መካሄዳቸውን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ2016 በጀት ዓመት የሩብ ዓመት አፈጻጸም አቅርቧል።
በሰላም ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ አቶ አዱኛ በቀለ ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት ሚኒስቴሩ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
በተለይ በሰባት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሆነም አብራርተዋል።
ከእነዚህ መካከል የመረጃ ተደራሽነትን ማስፋት፣ የሰላም እሴቶችን ማጎልበት፣ አገራዊ የሰላም ጉዳዮች ላይ ጥናቶችን ማካሔድ፣ ለዘላቂ ሰላም መፍትሔ የሚያመላክቱ ውይይቶችን ማካሔድ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
በዚህም በሩብ ዓመቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚያስችሉና መፍትሔን የሚያመላክቱ ውይይቶችን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ማካሄድ ተችሏል።
በዚህ የውይይት መድረክ ላይ በዘርፉ የተለያዩ ጥናቶችን ያካሔዱ 389 ሙሁራንና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት እንደነበርም አንስተዋል።
በተጨማሪም የሰላም እሴት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ብሔራዊ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይም እንዲሁ በሩብ ዓመቱ ከ3ሺህ በላይ በጎ ፍቃደኞችን በሁለት ዙር በማሰልጠን ወደ ተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ማሰማራት መቻሉንም አክለዋል።
በዋናነት በቴክኖሎጂ በተደገፈ የግጭት ቅድመ መከላከል ስራ ላይ በተከናወኑ ተግባራት 32 መረጃዎች ደርሰው ምላሽ እንደተሰጣቸውም ገልጸዋል።
ቋሚ ኮሚቴው በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ የስራ መመሪያ የሚሰጥ ይሆናል።