ተጠያቂነትን በማስፈን ሙስናን ለመከላከል የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት - ኢዜአ አማርኛ
ተጠያቂነትን በማስፈን ሙስናን ለመከላከል የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 21/2016 (ኢዜአ) ፦ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተጠያቂነትን በማስፈን ሙስናን ለመከላከል የሚያከናውነውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ።
"ሙስና የጋራ ጠላታችን ነው፤ በኅብረት እንታገል" በሚል መሪ ኃሳብ 20ኛው አገር አቀፍ የፍርድ ቤት ዘርፍ የፀረ-ሙስና ቀን የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት፣ የፌዴራል የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ምክትል ኮሚሽነር እሸቴ አስፋው፣ የፌዴራል ፍርድ ቤትና ተጠሪ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች፣ ዳኞችና ሌሎች አካላት ተገኝተዋል።
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ቴዎድሮስ ምህረት በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የሙስና ወንጀል የፍትሕ ተቋማትን አደጋ ላይ የሚጥል የሥነ-ምግባር ጉድለት ነው ብለዋል።
በመሆኑም የፍትሕ አካላት ሕዝብና መንግሥት የሰጣቸውን ኃላፊነት በፍጹም ታማኝነት በመወጣት ለአገራዊ የሙስና ትግል አዎንታዊ ሚና መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የፍትሕ ተቋማት በሙስና ወንጀል ተጋላጭነት የሚፈተኑ በመሆናቸው ጫናውን በመቋቋም አገራቸውንና ሕዝባቸውን በፍጹም ታማኝነት በማገልገል ተጠያቂነት እንዲሰፍን ለሚጫወቱት አዎንታዊ ሚና ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም የሙስና ተጋላጭነትን በመቀነስና ተጠያቂነትን በማስፈን ሙስናን ለመከላከል የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።
የፌደራል የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ምክትል ኮሚሽነር እሸቴ አስፋው፤ ሙስናን ለመከላከል የሃብት ምዝገባ፣ የተጋላጭነት ጥናት፣ የሥነ-ምግባር ግንባታና ግንዛቤ ፈጠራ ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በፍትሕ ተቋማት ላይ ያለውን የሙስና ተጋላጭነት የሚያመላክት የጥናት ውጤት መካሄዱን ጠቅሰው፥ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተጋላጭነት ጥናት ውጤቱን ተግባራዊ ለማድረግ የወሰደውን ተነሳሽነት አድንቀዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሥጋት እየሆነ የመጣውን የሙስና ወንጀል ለመከላከል ከፍትሕና ተጋላጭነት ከሚስተዋልባቸው ተቋማት ጋር በመተባበር ተጠያቂነት እንዲሰፍን እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በመድረኩም አገራዊ የሙስና ተጋላጭነትን፣ ዓለም አቀፋዊ፣ አሕጉራዊና ቀጣናዊ ተሞክሮዎችን የሚያመላክትና የፍትሕ ተቋማት የሙስና ተጋላጭነትን የሚሳዩ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ምክክር ተደርጎባቸዋል።