በአማራ ክልል በዘንድሮው የበጋ ወራት ለሚከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ከ376 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ተለይቷል

ባህርዳር ፤ ህዳር 21/2016(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በመጭው ጥር ወር ለሚጀመረው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ከ376 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የመለየት ስራ መከናወኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአፈር ለምነትን ለማሻሻልና የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

ለዚህም በዘንድሮው የበጋ ወራት ከ9 ሺህ በሚበልጡ ተፋሰሶች ለሚከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ከ376 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የመለየት ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።

በዚሁ የልማት ስራ ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚበልጡ አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉ ጠቅሰው፤ ከነዚህ መካከልም ማሳን በመለካት ለትግበራ የሚያዘጋጁ ከ299 ሺህ በላይ ቀያሽ አርሶ አደሮች መሆናቸውን ገልፀዋል።

ለቀያሽ አርሶ አደሮች በተግባር የታገዘ ስልጠና በየደረጃው ባሉ የግብርና ባለሙያዎች መሰጠት መጀመሩንም ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

ለልማት ስራውና ለቅየሳ ከሚያስፈልጉ ከአራት ሚሊዮን በላይ መሳሪያዎች ውስጥ እስካሁን ከግማሽ በላይ የሚሆነው መለየት መቻሉን አመልክተዋል።


 

ወቅታዊ የፀጥታ ችግሩ እንዳለ ቢሆንም የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራው የህልውና ጉዳይ ሆኖ በልዩ ትኩረት እንደሚከናወንም አስገንዝበዋል።

ለእቅዱ መሳካትም ባለድርሻ አካላት መረባረብ እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ አርሶ አደሩም ባለፉት ጊዜያት በተሰሩ ስራዎች የተገኘውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል ሲባል በልማት ስራው በስፋት መሳተፍ እንዳለበት አሳስበዋል።

በዘንድሮው ዓመት ለሚከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ መዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ በዋግህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የደሃና ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሞገስ ታደሰ ናቸው።

አካባቢያቸው በዝናብ እጥረት ለድርቅ የተጋለጠ በመሆኑ በየዓመቱ በበጋ ወራት ያከናወኑት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ በአካባቢው ተራቁቶ የነበረው መሬት ወደነበረበት እየተመለሰ መምጣቱን ገልጸዋል።

በዘንድሮው የበጋ ወቅት ለሚከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራም ከወዲሁ ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

በማእከላዊ ጎንደር ዞን ላይ አርማጭሆ ወረዳ የግንድ መጣያ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ንጉሴ ማሩ በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል ያለማናቸው ተፋሰሶች ለንብ ማነብና ለወተት ላሞች እርባታ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።  

''የተራቆቱ አካባቢዎች በአጭር ጊዜ እንዲያገግሙ በየዓመቱ የሚያከናውኗቸው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ የአፈር መሸርሸርን ማስቀረት እንደቻለ ተናግረዋል።

ከዚህም በላይ ለቤት እንስሳት መኖና ለንብ ማነብ ስራ አመቺ ሁኔታ በመፍጠሩ ዘንድሮም የልማት ስራው ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንደሚሆኑ ገልፀዋል።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት ከ7 ሚሊዮን ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ማከናወን እንደተቻለም የቢሮው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም