የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ለሶስት ተመራማሪዎች ሽልማት ሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ለሶስት ተመራማሪዎች ሽልማት ሰጠ
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 21/2016 (ኢዜአ) ፡- የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ለ21ኛ ጊዜ የቶሬ ጎዳል ሽልማትን ለሶስት ተመራማሪዎች አበርክቷል።
የቶሬ ጎዳል ሽልማት በጤናው መስክ የዶክተር ጎዳልን ዓለም አቀፍ ተጽእኖ ማሳያ ሆኖ የሚያገለግል የሽልማት መርኃ-ግብር መሆኑ ተመላክቷል።
ዶክተር ቶሬ ጎዳል የዛሬ ሀምሳ ዓመት ገደማ የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ሁለተኛው ዳይሬክተር ሆነው በሚያገለግሉበት ወቅት ኢትዮጵያውያን ወጣት ተመራማሪዎች ያለባቸውን ተግዳሮት ለመፍታት እና ለማበረታታት የጀመሩት የገንዘብ ሽልማት መሆኑም ተገልጿል።
በመርኃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ ፈጠራን ማሳደግ የተወሳሰቡ ችግሮችን በአዲስ እይታ ለመፈተሽ እና አዳዲስ መፍትሄዎችን ለማምጣት ዘላቂ ልማትን የሚያመጡ አማራጭ መንገዶችን ለማግኘት ይረዳል ሲሉ ገልጸዋል።
የቶሬ ጎዳል ሽልማት ወጣት ተመራማሪዎችን ለተሻለ ምርምር የሚያነቃቃና የእያንዳንዳቸው ውጤት አስተዋጽኦው ለሌሎች በር ከፋች በመሆኑ ሊበረታታና ሌሎችም ተሞክሮውን ሊጋሩት ይገባል ማለታቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
“የዶክተር ጎዳል እሴቶች እና መርሆዎች ለእኛ እንደ ትልቅ ማበረታቻ ሆነው በአገልግሎት ዘመናችን ሁሉ እንጠቀምባቸዋለን” ያሉት ደግሞ የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ናቸው፡፡
ሽልማቱ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት መምህር ዶክተር ያዴኖ ያዛቸው ታዬ፣ በአሪሲ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የላብራቶሪ ባለሙያ ዶክተር ሽመልስ ተሾመ አያልነህ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ረዳት መምህርት ወይዘሮ ሳሮን ፍቃዱ ተበርክቷል።
በሽልማት መርሃ-ግብሩ የኖርዌይና ስዊድን ኤምባሲ ተወካዮች፣ የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፣ የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት፣ የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ሆስፒታል አመራርና ሰራተኞች፣ የህክምና ተማሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።