ኢትዮጵያ በ28ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ የአረንጓዴ አሻራና ሌሎችም ተሞክሮዎቿን ታስተዋውቃለች

145

 

አዲስ አበባ፤ ህዳር 20/2016(ኢዜአ፦ኢትዮጵያ በዱባይ በሚካሔደው 28ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ የአረንጓዴ አሻራና ሌሎችንም ተሞክሮዎቿን ለዓለም እንደምታስተዋውቅ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ ገለጹ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባዔ (ኮፕ 28) በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፤ በዱባይ መካሄድ ጀምሯል።

ዶክተር ፍጹም ይሄንን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት በስፍራው ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው ኤግዚቢሽን በአረንጓዴ አሻራ ያስመዘገበችውን ስኬትና ሌሎችንም ተሞክሮዎች ለዓለም ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል።

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ስራዋን በአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ በተዘጋጀው የኢትዮጵያ አውደ ርእይ/ፓቪሊዮን/ በማስተዋወቅ ላይ መሆኗንም ገልጸዋል። 

በ1ሺህ 500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ትልቅ ኢግዚብሽን በማዘጋጀት ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በተጨባጭ ለውጥ እያመጣች መሆኗን የምናሳይበት ነው ብለዋል።

በጉባኤውም መሪዎች ንግግር በማድረግ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚዘጋጁ ስብሰባዎች ላይ በመሳተፍ በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ዙሪያ ድምጿን ታሰማለች ብለዋል። 

በዚህም በዘርፉ የተከናወኑ ስራዎችን በማስተዋወቅ ብሎም እያጋጠሙ በሚገኙ ተግዳሮቶች ዙሪያ የአፍሪካ ድምጽ በመሆን ትልቅ ተሳትፎ ይኖረናል ሲሉም ገልጸዋል። 

በዚህ ኤግዚቢሽንም በተለያዩ ዞኖች ማለትም የኢትዮጵያን አረንጓዴ አሻራ ኢንሼቲቭ እና ያስገኘውን ጥቅሞች በተመለከተ ለዕይታ ይቀርባል ብለዋል።

በተጨማሪም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በማጉላት ዘላቂ የግብርና ልማት ተሳትፎዎች ላይ በማተኮር  በስንዴ ልማት  እምርታዊ ለውጥ የታየበት ነውም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም