በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የሙስና ወንጀልን በጋራ መከላከል ይገባል- አቶ ታዬ ደንደዓ

167

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 20/2016 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት መሳካት የሙስና ወንጀልን በጋራ መከላከል ይገባል ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደዓ ገለጹ።

የሰላም ሚኒስቴር ሰራተኞች 20ኛውን ዓለም አቀፍ የጸረ-ሙስና ቀን በማስመልከት "ሙስና የጋራ ጠላታችን ነው፤ በሕብረት እንታገል" በሚል መሪ ሃሳብ የምክክር መድረክ ተካሂዷል። 

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ ታዬ ደንደዓ፤ በአንድ ሀገር የሙስና መስፋፋት ለበርካታ ችግሮች ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።


 

የሀገር የእድገት ጸርና የህዝቦች የምሬት ምክንያት ከመሆንም ባለፈ ለሰላምና መረጋጋት እንቅፋት መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያም የሙስና ወንጀል የሚያስከትለውን ችግር ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሙስና መከላከል ስራ ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ሁላችንም በጋራ መከላከል ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት መሳካት የሙስና ወንጀልን በጋራ መከላከል ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።


 

የፌዴራል ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እሸቴ አስፋው፤ የሙስና ወንጀል የበርካታ ችግሮች ምክንያት በመሆኑ የጋራ ትግልን የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

ኮሚሽኑ ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ ዘርፎችን በመለየት የመከላከልና የህግ ተጠያቂነትን ለማስፈን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

በመሆኑም በሁሉም ሴክተሮች ህብረተሰቡ የመከላከሉ ስራ አጋዥ በመሆን ሙስናን እንዲታገል ጥሪ አቅርበዋል።

የጸረ-ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ ባከናወናቸው ተግባራት 9 ቢሊየን ብር እና 4 ሚሊየን ካሬ ሜትር መሬትን ከሌብነት ማትረፍ እንደተቻለ መገለጹ ይታወቃል። 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመስከረም ወር የ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት የመክፈቻ ሥነስርዓት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መንግስት የሙስና መከላከል ስራን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸው ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም