የጤና መድህን አገልግሎትን ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቷል

166

ቦንጋ ፤ ህዳር 20/2016 (ኢዜአ) ፦ በሀገሪቱ የጤና መድህን አገልግሎት ስርዓትን በማጠናከር ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ገለጸ።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የ2016 ዓ.ም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የንቅናቄ መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።


 

በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ያምሮት አንዷለም እንዳሉት፤ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓት በርካታ የሀገሪቱ ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል።

በተለይም በከተማና በገጠር መደበኛ ባልሆነው የኢኮኖሚ ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ በማድረግ ዜጎች ያለምንም ስጋት የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ጉልህ ሚናን እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል።

በመሆኑም አገልግሎቱን ይበልጥ በማጠናከር ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ተደራሽ እንዲያደርግ ልምዶችን በመቀመር የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ከጀመረ ወዲህ የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ በተለይም ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ላሉ የህብረተሰብ ክፍሎች እፎይታን ፈጥሯል ብለዋል።

በቀጣይም አገልግሎቱን ከማጠናከር አንጻር የሚነሱ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የመድሃኒት አቅርቦትና ሌሎች ችግሮችን ለይቶ ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በተቀናጀ መንገድ እንደሚሰራ ገልፀዋል።

አገልግሎቱን የሚያገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ቁጥርና ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው የህዝብን ፍላጎት ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች እንደሚጠናከሩም ተናግረዋል።


 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በበኩላቸው በክልሉ አገልግሎቱን ለማጠናከር ያሉት ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት መፍትሄ ለመስጠት የንቅናቄ መድረኩ ማስፈለጉን ጠቁመዋል።

በክልሉ እስከ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ/ም ድረስ የነባር አባላት እድሳትን 95 በመቶ እንዲሁም አዲስ አባላትን የመመዝገቡ ሥራን ደግሞ 75 በመቶ ለማጠናቀቅ መታቀዱን ገልጸዋል።

መድረኩን የታደሙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ በላይ ተሰማ በበኩላቸው የጤና መድህን አገልግሎት ዜጎች ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ እያስቻለ በመሆኑ ሊጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።

አገልግሎቱ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸውና ዓመታዊ የጤና መድህን ወጪያቸውን መሸፈን የማይችሉ ዜጎች በመንግስት እንዲሸፈንላቸው በማድረግ ፍትሃዊነትን ያረጋገጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

በክልሉ ባለፈው ዓመት ብቻ ከ136 ሺህ በላይ የጤና ማህበረሰብ የጤና መድህን አባላት ከነቤተሰቦቻቸው በየደረጃው የህክምና አገልግሎት ማግኘታቸውም ተገልጿል።

የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት መድረክ ላይ ባለፈው ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ዞኖችና ወረዳዎች የዕውቅናና የምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን የቀጣይ ስራን ማጠናከር የሚያስችል ስምምነትም ተፈርሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም