የፌዴራል ድጎማ በጀት ቀመር ለማሻሻል በሚያስችሉ የቅድመ ዝግጀት ሥራዎች ላይ ውይይት ተካሄደ

116

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 20/2016 (ኢዜአ)፦በበቂ መረጃ የተደገፉ ስራዎችን ማከናወን ለፌዴራል ድጎማ በጀት ቀመር ማሻሻል ሂደት ቁልፍ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መሆናቸው ተገለጸ፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የድጎማ የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል ተቋማት ከፍተኛ ሃላፊዎች የፌደራል ድጎማ በጀት ቀመር ለማሻሻል በሚያስችሉ የቅድመ ዝግጀት ሥራዎች ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡

በመድረኩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላትና የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮችን ጨምሮ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ ከገቢዎች ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የክልሎችና የፌዴራል መንግሥት የጋራ ተብለው የተመደቡ ገቢዎች በሁለቱ መካከል የሚከፋፈሉበትን፤ እንዲሁም የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች ድጎማ የሚሰጥበትን ቀመር የመወሰን፤ ከሀገራዊ ኃላፊነቶቹ መካከል በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ምክር ቤቱም የተጣሉበትን ኃላፊነቶችና የወጡ ሕጎችን ተከትሎ የሕገ መንግሥት የበላይነት፣ ሕገ መንግስታዊነት፣ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት ሀገራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት የበኩሉን ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል በክልሎች መካከል ውጤታማና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልን ለማረጋገጥ የሚረዳ የፌዴራል ድጎማና የጋራ ገቢዎች ቀመር እንዲዘጋጅ በማድረግ፤ የማከፋፈያ ቀመሮቹ በፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልና በክልሎች የተመጣጠነ እድገት ላይ ያላቸዉን አንድምታ እንዲጠና በማድረግ ሰፊ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን አንስቷል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር አሁን ያለው ቀመርና አፈጻጸሙ እንደገና መፈተሽ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ከቋሚ ኮሚቴውና ከሚመለከታቸው የፌደራል ባለድርሻ አካለት ጋር ግብዓት ለመሰብሰብ የታለመ መድረክ ነው ብለዋል፡፡

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የፊስካል ፌዴራሊዝም ሪፎርም መደረጉንና በርካታ ውጤቶች የተገኙበት መሆኑን አስታውሰዋል፡፡


 

በቀጣይም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎችን በተገቢው የሕግ አግባብ ለመመለስ ቁርጠኝነት እንደሚፈልግና ለዚህም ሁሉም ባለ ድርሻ አከላት በርብርብና በእኔነት ስሜት ሊሰራ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡

በቀጣይ ለሚደረገው የቀመር ማሻሻል ስራ ከሚደረግ ቅድመ ዝግጅት ጋር ተያይዞ በጥናትና በበቂ መረጃ የተደገፉ ስራዎችን መስራት ለቀመር ማሻሻል ሂደት ቁልፍ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መሆናቸውንም አስገንዝበዋል፡፡

በመደረኩ የሚነሱ አስተያየቶችና ሀሳቦች ቋሚ ኮሚቴው ለሚያዘጋጀውና ለምክር ቤት ለሚቀርበው ሀገራዊ ሰነድ ትልቅ ግብዓት ሆኖ እንደሚወሰድም ነው የገለጹት፡፡

ለቀመር ዝግጅት የሚያስፈልጉ መረጃዎች ወቅታዊና ተአማኒነት ያላቸው እንዲሆኑ በቂ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ማከናወን እንደሚገባ የጋራ ስምምነት መደረሱን ተጠቅሷል።

በመረጃ አቅርቦት ረገድ ሃላፊነት የተጣለባቸው የፌዴራልና የክልል ተቋማት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አቅጣጫ መቀመጡን የፌዴሬሽን ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም