ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ የአገው ብሄረሰብ ቋንቋን ከማሳደግ በላይ ባህሉን ለማጎልበት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል

ሰቆጣ ፤ ህዳር 20/2016 (ኢዜአ) ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ የአገው ብሄረሰብ ቋንቋን ከማሳደግ በላይ ባህሉን ለማጎልበት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ገለጹ። 

በዞኑ 18ኛው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች  ቀን "ብዝሃነትና እኩልነት፤ለአገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ በደም ልገሳና በፓናል ውይይት ተከብሯል። 


 

የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ፋንታይቱ ካሴ እንዳሉት፤ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን መከበር የአገው ብሄረሰብ ማንነት እንዲንፀባረቅና እንዲታውቅ አድርጓል። 

ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ለብሄር ብሄረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር እድል ከመስጠቱም ባለፈ በቋንቋ መማርና መዳኘት እንዲችሉ ማድረጉን አስታውሰዋል። 

በተለይም የአገው ብሄረሰብን ታሪክ፣ ባህልና ማንነት በማጎልበት ትልቅ ለውጥ ማምጣት መቻሉን አፈ ጉባዔዋ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ብሄራዊ ማንነትን በማጎልበት ለሰላምና ሉዓላዊነት መከበር ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች በፅናትና በአንድነት ሊሰሩ እንደሚገባ አብራርተዋል። 

የአገርን አንድነትንና ሉዓላዊነትን አደጋ የሚጥሉ ጉዳዮችን በውይይትና በምክክር የመፍታት ባህል የማዳበር አስፈላጊነትንም ነው የጠቆሙት።

የበዓሉ ተሳታፊ ወጣት ገነት ሰፊው እንዳለችው፤ ፌዴራላዊ ስርዓቱ በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመማር እድልን ከመፍጠር ባሻገር ባህልና ማንነትን ለማንፀባረቅ ትልቅ ጠቀሜታ አስገኝቷል። 

"ወጣቱ ባህሉን ማንነቱን በአግባቡ ተረድቶ ህብረ ብሄራዊት አገርን ለመገንባት በሚደረገው ሂደት የበዓሉ መከበር ትልቅ ሚና አለው" ብላለች። 

"ከሚነጣጥሉን ትርክቶችና ከመገፋፋት ይልቅ አንድ በሚያደርጉ ትርክቶች መግባባት ያስፈልጋል" ያለችው ወጣት ገነት፤ ወጣቱ ለአገር ልማትና ለውጥ በእኩልነት መሰለፍ እንደሚገባ ገልፃለች።

“የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ኢትዮጵያዊያን በአንድነት እንድንቆም ትልቅ መሰረት የጣለ ነው” ያሉት ደግሞ የፃግብጅ ወረዳ ነዋሪ አቶ ሃብታሙ ደባሽ ናቸው። 

ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ “ባህልን ለማጎልበት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል” ብለዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም