የአካል ጉዳተኞች ቀን የፊታችን ሰኞ በአሶሳ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
የአካል ጉዳተኞች ቀን የፊታችን ሰኞ በአሶሳ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 20/2016(ኢዜአ)፦ዓለም አቀፉ የአካል ጉዳተኞች ቀን የፊታችን ሰኞ ኅዳር 24 ቀን 2016 ዓ.ም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአሶሳ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ተገለጸ።
እለቱን በማስመልከት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ እለቱ የሚከበረው አካል ጉዳተኞችን ከዘላቂ የልማት ስትራቴጂዎች ጋር በማስተሳሰር ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ማረጋገጥ እንዲቻል ግንዛቤ በመፍጠር መሆኑን ገልጸዋል።
አካል ጉዳተኞችን ከዘላቂ የልማት ስትራቴጂዎች ጋር በማስተሳሰር ሰብዓዊና ዴሞክራሲዊ መብት ማረጋገጥ እንዲቻል ግንዛቤ የሚፈጠርበት መሆኑን አንስተዋል።
የአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል አጠቃላይ ሕግ ለማፅደቅ ረቂቅ ሰነድ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጆ፤ እለቱ ሲከበር የአካል ጉዳተኞችን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሕዝብ ንቅናቄ በመፍጠር መሆኑን ተናግረዋል።
ዓለም አቀፉ የአካል ጉዳተኞች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ32ኛ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ "ለአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እና ዘላቂ የልማት ግቦች ስኬት ትርጉም ያለው ትብብር!" በሚል መሪ ሃሳብ ለ31ኛ ጊዜ የሚከበር ይሆናል።