በአዲስ አበባ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ በኦን ላይን ሆነዋል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 20/2016(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ በኦን ላይን መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡

በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ አመት ዕቅድ አፈጻጸሙን ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ ገምግሟል፡፡


 

የቢሮው ምክትል ሃላፊ መስፍን አሰፋ፤ በሩብ አመቱ አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን፣ የፍጆታ ምርት አቅርቦትን በማሳለጥና ህገ ወጥ ንግድን በመከላከል በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ 

የቢሮውን አገልግሎት አሰጣጥ ዘመናዊ በማድረግና ለደንበኞች እርካታ ለመፍጠር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ በኦን ላይን እንዲሰጥ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ በኦን ላይን መሆኑም የደንበኞችን እንግልትና ተጨማሪ ወጪ ያስቀረ መሆኑን ገልጸዋል።

የምርት አቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣምን ተከትሎ የሚከሰተውን የኑሮ ውድነት ለመቆጣጠር ነባር የእሁድ ገበያዎችን የማስፋት ተግባር መከናወኑን ገልፀዋል፡፡

አሁን ላይ የእሁድ ገበያ ማዕከላት ቁጥር 172 መድረሱን የገለጹት ምክትል ሃላፊው በተሰራው ስራ ህብረተሰቡ ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ማስቻሉን ገልጸል፡፡

የግብርና ምርቶች እጥረት እንዳያጋጥም በአምስቱ የመዲናዋ መግቢያ በሮች ዘመናዊ የግብርና ምርቶች ማዕከላት እንዲገነቡ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም በለሚ ኩራ፣ ኮልፌና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች የተገነቡት ዘመናዊ የገበያ ማዕከላት ግንባታቸው ተጠናቀው ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል  በተደረገ የክትትልና የቁጥጥር ስራ ከ10 ሺህ በላይ ህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም