የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የግብርና ዘርፉን በስፋት ለመደገፍ የሚያስችል የወለድ ተመን ማሻሻያ አደረገ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 20/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የግብርና ዘርፉን በስፋት ለመደገፍ የሚያስችል የወለድ ተመን ማሻሻያ ማድረጉን አስታወቀ።

ባንኩ በግብርና ዘርፍ በአነስተኛ፣ መካከለኛና የኮርፖሬት ፕሮጀክት ብድር 11 ነጥብ 5 በመቶ የማበደሪያ የወለድ ተመን ወደ 7 በመቶ ዝቅ አድርጓል።

በማሻሻያው በሊዝ ፋይናንስና በፕሮጀክት ፋይናንስ የብድር ሞዳሊቲ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶችን ማካተቱም ተመላክቷል።

ባንኩ ዛሬ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመላከተው ከምስረታው ጀምሮ ለግብርና ዘርፉ ትኩረት በመስጠት ሲደግፍ የቆየ የፖሊሲ ባንክ መሆኑን በመጥቀስ ግብርናውን ለማሻሻል መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ ማሳካት እንዲቻልና የግብርና ሴክተሩን በማነቃቃት በዘርፉ የግል ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት እና ለመሳብ የባንኩ የሥራ አመራር ቦርድ የወለድ ተመን ማሻሻያ ማድረጉን አሳውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባለፉት ዓመታት ባካሄደው ሪፎርም የነበሩበትን ተግዳሮቶች እየቀረፈና አዳዲስ አገልግሎቶችን ለደንበኞች እያቀረበ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ በመግለጫው የተመላከተ ሲሆን ይህ የወለድ ተመን ማሻሻያም ወቅቱን የጠበቀ እና በአገራችን ያለውን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ማዕከል ያደረገ መሆኑን አብራርቷል፡፡

ባንኩ የወለድ ተመን ማሻሻያ ማድረጉን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው እንዳሉት፣ “የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ ያላትን ከፍተኛ የሆነ ያልታረሰ የመሬት ሀብት ወደ ስራ ለማስገባት፤ ባለሀብቶች፣ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች የበለጠ እንዲበረታቱ ለማድረግ በግብርና ዘርፍ በአነስተኛ፣ መካከለኛና የኮርፖሬት ፕሮጀክት ብድር ለሚጠይቁ ይጠበቅ የነበረው የ11.5 በመቶ የማበደሪያ የወለድ ተመን ወደ 7 በመቶ ዝቅ አድርጓል።”

ባንኩ ስራ ላይ ያዋለው ይህ ማሻሻያ ዘርፉን ለማሳደግ ያቀደው ስትራቴጅያዊ ሪፎርም አካል ሲሆን፣ መንግስት የግብርና ዘርፉን ለማሳደግ እየሰራ ያለውን ስራ የበለጠ የሚያግዝ መሆኑንም ገልፀዋል።

ባንኩ የወለድ ተመን ማሻሻያ ማድረጉ በአምራች ዘርፉ የተሰማሩ ድርጅቶች በጥሬ እቃ አቅርቦት እጥረት ምክንያት የነበረባቸውን ዝቅተኛ የማምረት አቅም በማሻሻልና በውጭ ምንዛሬ የሚገቡ ምርቶችን ለመቀነስ ከመርዳቱም በላይ ሀገራችን በዘርፉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ የሚያግዝ መሆኑም ተብራርቷል።

በተጨማሪም የተደረገው የወለድ ተመን ማሻሻያ የምግብና የኢንዱስትሪ ሰብሎች ላይ ያተኮረ ሥራ በኢንቨስተሩ እንዲሰራ የሚያበረታታ ሲሆን፣ የምግብ ፍላጎትንና ለኢንዱስትሪ የሚሆኑ የጥሬ ዕቃዎች አቅርቦት ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ምርቶች ከማሟላት ጎን ለጎን፣ የምግብ ዋጋ ንረትን ለማረጋጋትና የውጭ ምንዛሬ አቅምን ለማሳደግ እንደ መንግስት እየተሰራ ያለውን ስራ እንደሚያጠናክር ይጠበቃል።

ለከፍተኛ፣ ለአነስተኛና መካከለኛ የግብርና ፕሮጀክቶች የተደረገው የማበደሪያ ወለድ ምጣኔ ማሻሻያ ባንኩ ለዘርፉ ዕድገት ያለውን ቁርጠኛ አቋም ያሳየበት መሆኑም በመግለጫው ተመላክቷል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሀገራችንን ኢኮኖሚያዊ ልማት በተሻለ ደረጃ እንዲረጋገጥ አሁን በገበያው ውስጥ ካለው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት በተመረጡ ዘርፎች ለተሰማሩ እና ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለሚያንቀሳቅሱ ተበዳሪዎች በሌሎች አገልግሎቶች ላይ መጠነኛ የወለድ ተመን ማሻሻያ ማድረጉ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም