በህብረ-ብሄራዊ ማንነት ለተሳሰረ ህዝብ ፌዴራሊዝም ሁነኛ መፍትሔ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በህብረ-ብሄራዊ ማንነት ለተሳሰረ ህዝብ ፌዴራሊዝም ሁነኛ መፍትሔ ነው
ቦንጋ ፤ህዳር 20/2016 (ኢዜአ):- በሀገሪቱ ብዝሃነትን ለማስተናገድና ሰላምና ልማትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የፌዴራል ሥርዓት ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለፁ።
"ብዝሃነትና ዕኩልነት ለአገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ የዘንድሮው 18ኛው የብሔር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ዳይሬክተር ዶክተር ዬረቾ ብርሃኑ እንዳሉት፤ በአገራችን የፌዴራል ሥርዓትን ህብረ-ብሄራዊ አንድነትን ለማጠናከር ሁነኛ መፍትሔ ነው።
ራስን በራስ የማስተዳደር ስርዓትን በማበጀት በልዩ ልዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚነሱ ጥያቄዎች ዘላቂ ምላሽ እንዲያገኙና ማንነታቸው ተከብሮ እንዲኖሩ የሚያስችል መሆኑንም ተመራጭ እንዳደረገው አንስተዋል።
አገርን ሊገልፅ የሚችል የተለያየ ማንነት ያላቸው ተማሪዎችን የያዙት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የፌዴራሊዝም ስርዓት መሬት እንዲይዝ ከማድረግ አኳያ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባም አንስተዋል።
''ወጣቱ ትውልድ ብዝሃ ማንነትን በመረዳት ሃላፊነቱን እንዲወጣ ማድረግ ይጠበቅብናል'' ያሉት በዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ልዩ ረዳት አቶ ጌትነት ገብረሚካኤል ናቸው።
በክብረ በዓሉ ላይም ዕለቱን አስመልክቶ የተሰናዱ ልዩ ልዩ ስፖርታዊ ውድድሮችና ኪነ ጥበባዊ መርሃ ግብሮች ተስተናግደዋል።