በኢትዮጵያ ለመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ወጥነት ያለው የአሰራር መስፈርትና የህግ ማዕቀፍ ሊዘጋጅ ነው

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 20/2016 (ኢዜአ)፦ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በሀገሪቱ የመስኖ ልማት ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ያለመ  ወጥነት ያለው የአሰራር መስፈርትና የህግ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት የአንድ ዓመት ፕሮጀክት ይፋ አደረገ።

ከዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የሚተገበረው ይህ ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደሚከናወን ተገልጿል።


 

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትሯ ኢንጅነር አይሻ መሀመድ በዚህ ወቅት እንዳሉት በመስኖ መሰረተ ልማት  ግንባታዎች ጥናት፣ ዲዛይንና ጥገና ረገድ አሁንም ተግዳሮቶች አሉ።

ለአብነትም በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ የአቅም ውስንነት፣ የሕግ ማዕቀፍ፣ የጥራት እንዲሁም በተያዘላቸው ጊዜ ገደብና በጀት አለመጠናቀቅ ከሚስተዋሉ ችግሮች ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ወጥ አሰራር እና መመሪያ ባለመኖሩ 75 በመቶ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች በዲዛይን ጥራት ችግር እንደሚጓተቱ ጠቁመዋል።

ይህን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍም የሀገሪቷን ነባራዊ ሁኔታ እና ተፈጥሯዊ ሀብት ያገናዘበ የመስኖ ልማትን ለመደገፍ ወጥነት ያለው የአሰራር  መስፈርት፣ መመሪያና የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት እንዳስፈለገ ገልጸዋል።

ይህን እውን የሚያደርግና በአንድ ዓመት የሚጠናቀቅ ፕሮጀክት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ዛሬ ይፋ መደረጉን ጠቁመዋል።



የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፣ ዩኒቨርሲቲው ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ አጠናቆ ለማስረከብ ሃላፊነቱን በአግባቡ እንደሚወጣ ገልጸዋል።

በቀጣይም በሀገራዊ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ዙሪያ የሚያደርገውን ሙያዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያመላከቱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም