በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ከ44 ሚሊዮን ብር በላይ ቦንድ ሽያጭ ተከናወነ 

ጭሮ ፤ ህዳር 20/2016 (ኢዜአ)፦በምዕራብ ሐረርጌ ባለፉት ሁለት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ከ44 ሚሊዮን ብር በላይ ቦንድ ሽያጭ መከናወኑን የዞኑ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

  የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ፈሪድ ይስሃቅ ለኢዜአ እንደገለጹት ቦንዱን የገዙት የዞኑ መንግሥት ሠራተኞች፣ አርሶ አደሮች፣ ነጋዴዎችና ባለሀብቶች ናቸው።


 

በዞኑ በወራቱ ለመሸጥ የታቀደው 40 ሚሊዮን ብር ቦንድ ቢሆንም፣ ሕዝቡ ባደረገው የተሻለ ተሳትፎ ክንውኑ የአራት ሚሊዮን ብር በብልጫ መመዝገቡን አስታውቀዋል፡፡

የዞኑ ሕዝብ በግል እስከ 200 ሺህ ብር ድረስ ዋጋ ያለው ቦንድ በመግዛት ያደረገው ተሳትፎ የሚያስደስትና ይበል የሚያሰኝ መሆኑንም ሃላፊው ገልጸዋል፡፡

በቦንድ ግዥው ከተሳተፉ የዞኑ ነዋሪዎች መካከል የመንግሥት ሠራተኛዋ  ወይዘሮ ወሲላ መዬ በአንድ ወር ደሞዛቸው ቦንድ በመግዛት ሀገራዊ ግዴታቸውን መወጣታቸውን ተናግረዋል።


 

በተጨማሪም "የ500 ብር ቦንድ በመግዛት የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አስተዋጽኦ በማድረጌ ደስታ ተሰምቶኛል" ብለዋል፡፡

የመንግሥት ሠራተኞችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ለህዳሴው ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል ወይዘሮ ወሲላ፡፡


 

የሒርና ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኮሌጅ ዲን አቶ ሽመልስ ታከለ በበኩላቸው ተቋሙ ሰሞኑን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል የ15 ሺህ ብር ቦንድ መግዛቱን ተናግረዋል፡፡

የኮሌጁ ማህበረሰብ የግድቡ ግንባታ ፍጻሜ እስኪያገኝ ድረስ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

ከዞኑ ባለፈው በጀት ዓመት ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም