የሕዳሴውን ግድብ ከዳር ለማድረስ ቦንድ መግዛታችንን እንቀጥላለን--የጅማ ባለሀብቶች - ኢዜአ አማርኛ
የሕዳሴውን ግድብ ከዳር ለማድረስ ቦንድ መግዛታችንን እንቀጥላለን--የጅማ ባለሀብቶች
ጅማ ፤ ህዳር 20/2016 (ኢዜአ)፦የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከዳር ለማድረስ በቦንድ ግዢ የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንደሚያጠናክሩ የጅማ ከተማ ባለሀብቶች ገለጹ።
በከተማዋ በትናንትናው ዕለት ብቻ ለግድቡ ግንባታ የ20 ሚሊዮን ብር ቦንድ ሽያጭ ተከናውኗል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው ቦንድ የገዙ ባለሀብቶች እንደተናገሩት በኢትዮጵያውያን የጋራ ትብብር የተጀመረው ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክት በትብብር ለማስፈፀም ተሳትፏቸውን ያጠናክራሉ።
ግድቡ ኢትዮጵያዊያንን በአንድነት ያስተሳሰረ፣ የኅብረታችን ውጤትና የአንድነታችን ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከባለሀብቶቹ መካከል የ600 ሺህ ብር ቦንድ የገዙት ወይዘሮ ሮዛ ቢያ ''ሀገራችንን ለማሳደግና የተሻለ የኑሮ ደረጃ እንዲኖረን በሀገር ልማት መሰተፍ ያስፈልጋል'' ብለዋል።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች እንዲሁም ህብረተሰቡ የሕዳሴውን ግድብ በኅብረት እንደጀመርነው ሁሉ በኅብረት ማጠናቀቅ አለብን ብለዋል።
"ግድቡ ለሀገሪቱ በቂ ኤሌክትሪክ በማመንጨት በሕዝቡ ሕይወት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት ያስችላል ብዬ አምናለሁ'' ሲሉም ባለሀብቷ ተናግረዋል።
ሌላኛው ባለሀብት አቶ በድሩ ሰማን በበኩላቸው የሀገሪቱ ብሩህ ተስፋ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከፍጻሜ ለማድረስ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በዚህኛው ዙር የ300 ሺህ ብር ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረጋቸውንና በቀጣይም ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል።
የኤሌክትሪክ ሃይል ልማትና አገራዊ ዕድገትን ለማፋጠን ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ባለሀብቱ፤ ዜጎች የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ ርብርብ ማድረግ አለብን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
"የሀገር ተስፋ ለሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረግ ይኖርብናል" ያሉት ደግሞ የ50 ሺህ ብር ቦንድ የገዙት ሌላዋ ባለሀብት ወይዘሮ አሚና አባነጋ ናችው።
እሳቸውም ከዚህ በፊት ቦንድ በመግዛት የዜግነት `ሃላፊነታቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን ገልጸው፣ ለወደፊትም ተጨማሪ ቦንድ በመግዛት ተሳትፎ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
መላው ኢትዮጵያውያን በአንድነትና በትብብር የጀመርነውን የግድቡን ግንባታ እስከ ፍጻሜው ማድረስ ይጠብቅናል በማለትም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።