በሀገር ልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት የወጣቶች ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ

180

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 20/2016 (ኢዜአ)፦በሀገር ልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት የወጣቶች ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል አንዳለበት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ተናገሩ።

የአፍሪካ ወጣቶች ወር የማጠቃለያ መርኃ ግብር የወጣቶችን ስብዕና እና ተጠቃሚነት በሚያሳድጉ ጉዳዮች ላይ በማተኮር በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያግዙ ተግባራትና በስብዕና ግንባታ ላይ አበረታች እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በሀገር ልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት የወጣቶች ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

በስብዕና ግንባታ፣ በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር ከማድረግ ባለፈ ወጣቶች በሀገራዊ ጉዳዮች የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እለቱን በማስመልከት ግንዛቤ የተፈጠረበት መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ከአባቶቻቸው የወረሱትን የጀግንነትና የጽናት መንፈስ በመላበስ ለአፍሪካ ብልጽግና ምሳሌ መሆን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ወጣቶች ችሎታቸውንና ፈጠራቸውን ለበጎ ነገር መጠቀም ከቻሉ የአህጉሪቷን ብሩህ ተስፋ ማለምለም የሚችል እምቅ ጉልበት እንዳላቸው አስረድተዋል።


 

16ኛው የአፍሪካ ወጣቶች ወር የማጠቃለያ መርኃ ግብር "ድንበር ተሻጋሪ የወጣቶች እንቅስቃሴ ለፓን-አፍሪካኒዝም" በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም