የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ በማጉላትና ብሔራዊ ጥቅሟን በማስከበር የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ

279

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 20/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ በማጉላትና ብሔራዊ ጥቅሟን በማስከበር ሂደት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ በሚኖረው ፋይዳ ላይ ከተለያዩ የሲቪል ድርጅት ተወካዮች ጋር ምክክር ተካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፤ የኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀል ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል ያደረገ ስለመሆኑ አብራርተዋል።

የብሪክስ አባል መሆን በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በአማራጭ የልማት ፋይናንስ ምንጭ ማስፋት እና አጋርነትን ለማጎልበት የሚረዳ መሆኑንም አንስተዋል።

ብሪክስ የሁሉም አመለካከት ማዕከልና በዓለም ትልቅ ምጣኔ ኃብታዊ ጉልበት ያለው ስብስብ መሆኑንም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ድምጿን ለማሰማት ተጨማሪ ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ ትልቅ ዲፕሎማሲ ስኬት መሆኑን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ብሪክስን የተቀላቀለችው ከየትኛውም ርዕዮተ-ዓለም ጎራ ለመወገን ሳይሆን፤ ከሁሉም የዓለም አገራት ጋር የጋራ ልማትን ለማረጋገጥ እና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ መሆኑንም አምባሳደር ምስጋኑ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የገፅታ ግንባታ እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዕውቅና እንዲያገኝ በማድረግ ረገድ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የላቀ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰው፤ የተዘጋጀው መድረክም ዋነኛ ዓላማ በብሪክስ ዙሪያ ሰፊ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል ነው ብለዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ በማጉላትና ብሔራዊ ጥቅሟን በማስከበር ሂደት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።


 

የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ፤ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች የውጭ ጉዳይን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ለሀገር አስተዋጽዖ እያበረከቱ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

በብሪክስ አባልነት ጉዳይ ግንዛቤ መፈጠሩም ማኅበራቱ የበኩላቸውን ሚና በላቀ መልኩ እንዲወጡ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት ጥያቄ በይፋ ተቀባይነት ያገኘው ባሳለፍነው ወርኅ ነሐሴ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የብሪክስ አባል ሀገራት 15ኛ ጉባዔ መሆኑ ይታወቃል። 

ኢትዮጵያን ጨምሮ ቡድኑን አዲስ የተቀላቀሉ አገራት ከመጪው የፈረንጆች አዲስ ዓመት መባቻ ጀምሮ የብሪክስ ሙሉ አባልነትን የሚያረጋግጡ ይሆናል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ዶክተር የቻለ ደጉ፤ ብሪክስ የሲቪክ ማኅበረሰብ አወቃቀር ላይ ወደፊት አማራጭ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልፀዋል።

በአባል ሀገራት ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ጥበቃ ሚናቸውን እንዲወጡም ብሪክስ ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ ትነበብ ብርሃኔ፤ ኢትዮጵያ ወደ ብሪክስ መግባቷ ለልማትና አጋርነት መጎልበት የሚጠቅም በመሆኑ መልካም ዕድል መሆኑን ገልፀዋል።

አባል ሀገራት በየራሳቸው የጋራ ስምምነት የሚመሩበት ስብስብ በመሆኑ ብሔራዊ ጥቅሞች እንደተጠበቁ ሆነው በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አቅም ግንባታ ላይም በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በፐብሊክ ዲፕሎማሲው መስክ ለኢትዮጵያ ገጽታ ግንባታና ልማት መጎልበት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም