የብሔር ብሔረሰቦች በዓል መከበሩ የብሔረሰቦቹን ማንነት ከማሳወቅ ባለፈ ለህገ መንግስት አስተምህሮ የተሻለ እድል ፈጥሯል

139

ህዳር 20/2016(ኢዜአ) ፡- የብሔር ፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል መከበር የብሔረሰቦቹን ማንነት ከማሳወቅ ባለፈ በህገመንግስት አስተምህሮ ላይ ጉልህ ድርሻ እንዳለው የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ገለጸ።

የኦሮሚያ ክልል የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በተለያዩ ተግባራትና የስራ ጉብኝቶች እንደሚከበርም ገልጿል።  

ክልሉ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚከበረው በዓል ባለው ተሳትፎና በክልሉ ደረጃ የአከባበር መርሃ ግብሩን አስመልክቶ የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት(ጨፌ ኦሮሚያ) ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።

የጨፌ ኦሮሚያ ምክትል አፈ ጉባዔ አቶ ኤሊያስ ኡመታ በመግለጫቸው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የብሔሮቹ የቃል ኪዳን ሰነድ የሆነው ህገ መንግስት የጸደቀበትን ታሳቢ ተደርጎ የሚከበር መሆኑን አንስተዋል።

ቀኑ ለተከታታይ ዓመታት በመከበሩ ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያስገኛቸው በርካታ ትሩፋቶች እንዳሉ ጠቁመዋል።


 

በተለይም በዓሉ የብሔረሰቦቹን ማንነት በአደባባይ በማውጣትና በፌዴራሊዝም እና ህገ መንግስታዊ አስተምህሮቱ ላይ ያስገኛቸው ግንዛቤዎችን በማከል።

ክልሉ የዘንድሮውን በዓል ከወትሮው በተለየ በልዩ ልዩ ተግባራትና በስራ ጉብኝት እንደሚያከብር ያነሱት አቶ ኤሊያስ፤ በተለይም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተከናወኑ ተግባራትን ማየትና ህብረተሰቡን ለበለጠ የልማት ተግባራት ማንቀሳቀስ ከበዓሉ መርሃ ግብር ዋነኛው መሆኑን አውስተዋል።

ህብረተሰቡ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ማድረግ፣ የፓናል ውይይቶች፣ ልዩ ልዩ ባዛርና ዐውደ ርዕይ፣ ነጻ የጤና አገልግሎትና የደም ልገሳ እንዲሁም ማስ ስፖርት ከመርሃ ግብሮቹ መካከል ተጠቃሾች ናቸው።

የኦሮሚያ ክልል የህዝቡን ባህልና እሴት የሚያንጸባርቁለትን ልዑካን ይዞ ጅግጅጋ በሚከበረው በዓል ላይ ለመሳተፍ ዘርፈ ብዙ ዝግጅቶችን ማጠናቀቁን ያነሱት አቶ ኤሊያስ ፤ ለዚህም አንድ አብይ ኮሚቴና ልዩ ልዩ ንዑሳን ኮሚቴዎች አስቀድመው መዋቀራቸውን ተናግረዋል።

በዓሉን ለመታደም ክልሉን አቋርጠው ለሚያልፉ ብሔር ብሔረሰቦች መልካም አቀባበል፣ መስተንግዶና ሽኝት እንደሚደረግ አንስተው፤ በዚህ አጋጣሚ ህዝቡ ወንድምነቱን፣ ፍቅሩንና መልካም እሴቱን አጉልቶ እንዲያንጸባርቅ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም