በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰፈነውን ሠላም በመጠበቅ የህዝብን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ-አቶ አሻድሊ ሃሰን

147

ግልገል በለስ፤ ህዳር 20/2016 (ኢዜአ) ፦በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰፈነውን ሠላም በመጠቀም የህዝብን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን ገለጹ።

በክልሉ 18ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ማጠቃለያ በዓል በመተከል ዞን ግልገልበለስ ከተማ ዛሬ ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ እንዳሉት ህብረተሰቡ፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ፖሊስና ሌሎች በከፈሉት መስዋዕትነት በመተከል ዞን ሰላምና መረጋጋት ሰፍኗል።

በአካባቢው የተረጋገጠውን ሰላም ተከትሎም በግለሰቦች ያለአግባብ የተያዙ ሰፋፊ መሬቶችን በማስለቀቅ ለሚያለሙ ግለሰቦች እንዲተላለፍ መደረጉን ገልጸዋል።

"በዚህም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ተግባራት ለማከናወን ተችሏል" ብለዋል።

የአካባቢውን የተፈጥሮ ፀጋ በተሻለ አልምቶ ወደ ሀብት በመቀየር የክልሉን ህዝብ ብሎም አገርን ወደ ብልጽግና ማሻገር የክልሉ ዋነኛና ቀዳሚ ተግባር ተድርጎ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

"የክልሉን ህዝብ ከልማት የተሻለ ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻለው የሰፈነው ሰላም ተጠናክሮ ሲቀጥል ነው" ያሉት አቶ አሻድሊ፣ ቀደም ሲል በዞኑ ተከስቶ ነበረው የሠላም እጦት እንዳይደገም ሁሉም ለሰላም ዘብ መቆሙን እንዲያጠናከር አሳስበዋል።

የልማት ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በአብሮነት መንቀሳቀስ እንደሚገባ አቶ አሻድሊ ጠቅሰው፣ "ለዚህም ከሚበታትኑን ይልቅ እንደ ሀገር አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይገባናል" ሲሉ አስገንዝበዋል።


 

የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ዶክተር ተመስገን ዲሳሳ በበኩላቸው በክልሉ የዴሞክራሲ ተቋማት ሃላፊነታቸውን በገለልተኝነት እንዲወጡ በማድረግ ዴሞክራሲን ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። 

መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን ውጤታማነት ለመከታተል ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ዋና አፈጉባኤው አመልክተዋል።

የክልሉ ህብረተሰብ የማንነቱ መገለጫ የሆኑ እሴቶቹን ጠብቆ ከማሳደግ ባለፈ ከሌሎች የአገሪቱ ህዝቦች ጋር ህብረብሔራዊ አንድነቱን ማጠናከር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

"በመተከል ዞን የሰፈነው ሰላም ለዞኑ ልማት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል" ያሉት የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ለሜሳ ዋውያ በበኩላቸው፣ የዞኑ አመራሮችና ባለሙያዎች ለመልሶ ግንባታ ርብርብ እያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል።

ባለሀብቱ ወደዞኑ በመግባት በእርሻ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና ሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሠማራም ዋና አስተዳዳሪው ጥሪ አቅርበዋል።

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል አቶ አወድ ሙሳ ከዚህ በኋላ የመተከል ዞን ብሎም የክልሉ ሠላም እንዲታወክ እንደማይፈልጉ ገለጸው፣ "በአካባቢው የሰፈነውን ሰላም ለማጠናከር የበኩሌን እወጣለሁ" ብለዋል።


 

ወይዘሪት ትዕግስት ዲቢሳ በበኩሏ እንዳለችው ባለፉት ዓመታት በተከበሩ የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል የማንነት መገለጫ የሆኑ እሴቶቾ ጎልተው ወጥተዋል።

በዓሉ እርስ በርስ ለመተዋወቅና አብሮነትን ለማጠናከር ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቁማ፣ በዓሉን ለኢኮኖሚ ጠቀሜታ በማዋል በኩል ተጨማሪ ሥራ ያስፈልጋል ብላለች።

በዓሉ "ብዝሃነት እና እኩልነት ለአገራዊ አንድነት" በሚል መርህ በግልገል በለስ ስታዲየም ሲከበር የብሔር ብሔረሰቦች ሙዚቃና ስፖርታዊ ውድድሮች ቀርበዋል።

ለበዓሉ ስኬት የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትም ሽልማት ተሰጥቷል።

በበዓሉ ላይ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ የመተከል ዞንና የግልገል በለስ ከተማ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም