የቺካጎ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ስድስት ተቀራራቢ ፕላኔቶች ማግኘታቸውን ገለጹ 

241

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 20/2016 (ኢዜአ)፦ ስድስት ተቀራራቢ ፕላኔቶች ማግኘት መቻላቸውን በአሜሪካ የቺካጎ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች አስታወቁ።

ተገኙ የተባሉት ፕላኔቶች በራሳቸው የጸሃይ ስርአት ዙሪያ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ስርአቱን የጠበቀና ሙዚቃዊ ስልት ያለው መሆኑንም ተመራማሪዎቹ ይፋ ባደረጉት ምስል ገልጸዋል።

ኤች ዲ 110067 የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ፕላኔቶቹ ኮማ ቤሬኒሲስ ከተባለው የህብረ ክዋክብት ስብስብ በአንድ መቶ የብርሃን አመታት ይርቃሉ መባሉን ኔቸር የተባለውን የምርምር መጽሄት ጠቅሶ ዩ ፒ አይ  በድረ ገጹ አስነብቧል።

የፕላኔቶቹ መገኘት ስለፕላኔቶች አፈጣጠር እና ዝግመተ ለውጥ አዲስ እይታ ሊፈጥር ይችላል የሚሉት የጥናት ቡድኑ መሪ ራፋኤል ሊዩክ “መሰል ግኝቶች ኔፕቱን በተባለችው ፕላኔት ዙሪያ ያሉ አካላት እንዲታወቁ እድል ይፈጥራል” ማለታቸውን ዘገባው አስታውሷል።

“ምድር ካለችበት የጸሃይ ስርአት ውጪ ያሉ ሌሎች ፕላኔቶች አፈጣጠር፣ ቆይታ፣ የተሰሩበት ነገር ውሃ ስለመያዛቸው እና ሌሎች ጉዳዮች የጥናቱ መነሻ እንዲሆን አስችሏል” ብለዋል ተመራማሪው።

የአሜሪካው ብሄራዊ የጠፈር ምርምር ኤጀንሲ ናሳ ከአውሮፓ የጠፈር ጥናት ድርጅት ጋር በመሆን በተላኩት ሳተላይቶች የክዋክብቱን የብርሃን መጠን፣ ከሌሎች ከዋክብት ጋር ያላቸውን መስተጋብር መመልከት እንደተቻለም ተገልጿል።

እንደ ተመራማሪዎቹ ገለጻ ፕላኔቶቹ እርስ በእርስ ያላቸውን ርቀት የሚያስጠብቁበት ሬዞናንስ የተባለው ስርአት ያላቸው በመሆኑ በጸሃይ ዙሪያ ያሉት በርካታ ክዋክብት በሚያደርጉት መሽከርከር የሚጋጩባቸው አጋጣሚዎች በእጅጉ አናሳ መሆኑን በዘገባው ተመላክቷል። 


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም