ለአካባቢያችን ዘላቂ ሰላም የድርሻችንን እንወጣለን - የተሃድሶ ሰልጣኞች 

ደሴ፤ህዳር 20/2016 (ኢዜአ)፦  በተሃድሶ ስልጠና ያገኘነውን ዕውቀት ተጠቅመን ለአካባቢያችን ዘላቂ  ሰላም  የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ በኮምቦልቻ ጮሬሳ ጊዜያዊ ማቆያ የተሃድሶ ስልጠና ያጠናቀቁ  ግለሰቦች  ገለጹ። 

በምስራቅ አማራ ኮማንድ ፖስት የኮምቦልቻ ጮሪሳ ጊዜያዊ ማቆያ የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ ግለሰቦች ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅለዋል።

ከሰልጣኞቹ መካከል አቶ ታደሰ ግዛው በሰጡት አስተያየት፤  በጊዜያዊ ማቆያው ስለ አማራ ክልል አሁናዊ ሁኔታ በትክክል ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በተለይ ስለ ሰላም አስፈላጊነት፣ ስለ አብሮነትና የግጭት አስከፊነት በስልጠናው በቂ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ጠቁመው፤ ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

''በቆይታዬ ሰብዓዊ መብቴ ተጠብቆ ቆይቻለሁ፤ ከስህተታችን ተምረናል ለዘላቂ ሰላም መሰፈን ራሳችንን አዘጋጅተናል'' ብለዋል።

አቶ የአብቃል ቢታው በበኩላቸው፤ በቆይታቸው ሰብዓዊ መብታቸው ተጠብቆ ትምህርት ማግኘታቸውን አመልክተዋል።

ስለ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታና አብሮነት የተሰጣቸው ስልጠናም አሁን ያጋጠመውን ችግር በትክክል ተገንዝበው ለዘላቂ ሰላም የድርሻቸውን ለመወጣት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የተፈጠረላቸው ግንዛቤ በመጠቀም የተሳሳቱትን ወደ ሰላም እንዲመጡ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

''ከተሃድሶ ስልጠናው ያገኘሁትን ዕውቀት ተጠቅሜ ስለ ሰላምና አብሮነት አስተምራለሁ ያለችው'' ደግሞ ወይዘሪት ጤና ጌትነት ናት።

''ሰላም ከራስ፣ ከቤተሰብና ከአካባቢ እንደሚጀምር ተገንዝቢያለሁ፤ ቤተሰቦችን በማስተማር ሁሉም ለሰላም ዘብ እንዲቆሙ የድርሻዬን እወጣለሁ'' ብላለች።



 

በፌዴራል ፖሊስ የሰሜን ምስራቅ ሬጅመንት አምስት ሻለቃ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ኩራባቸው እንዳለ እንደገለጹት፤ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የተሳሳቱትን ግለሰቦች በማስተማር የመመለስ ስራ እየተካሄደ ነው።

እንዲሁም ሰልጣኞች በቆይታቸው የአገሪቷን ነባራዊ ሁኔታ በማሳወቅ ለአካባቢያቸው ሰላም ዘብ እንዲቆሙ ግንዛቤ እንዲያገኙ መደረጉን አስረድተዋል።

ሰልጣኞች ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉም ሰለ ሰላም በማስተማር የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

"እርስ በእርስ እያጋጩ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ችግር የሚፈጥሩትን ሁላችንም መታገልና ማውገዝ ይኖርብናል'' ያሉት ደግሞ በፌዴራል ፖሊስ ሰሜን ምስራቅ መምሪያ ምክትል አዛዥ ኮማንደር ሰይድ እንድሪስ ናቸው።

ሰልጣኞች በቆይታቸው ያገኙትን እውቀትና ግንዛቤ በመተግበር ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን  በንቃት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም