ቀጥታ፡

አብሮነታቸውን አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ በጅማ ከተማ  የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ታዳሚዎች ተናገሩ 

ጅማ፤ ህዳር 20/2016 (ኢዜአ) ፦በመተሳሰብ  የቆየውን አብሮነታቸውና አንድነታቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻቸውን እንደሚወጡ በጅማ ከተማ ዛሬ በተከበረው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ላይ  አስተያየታቸውን የሰጡ ታዳሚዎች ገለጹ።

በዓሉ በጅማ ከተማ የተከበረው “ብዝሃነትና እኩልነት ለሀገራዊ  አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀ ህዝባዊ ውይይት ነው።


 

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ወይዘሮ እመቤት ቃሲም በሰጡት አስተያየት፤ በጅማ ከተማ ህብረተሰቡ ተከባብሮ  በአብሮነትና በፍቅር እየኖረ መሆኑን  ተናግረዋል።

ይህንኑ አጎልብተው በመተሳሰብ አብሮነታቸውንና አንድነታቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

አቶ ተስፋዬ ወልደሰንበት በበኩላቸው፤ ጅማ የሰላም፣ የመተባበርና የፍቅር ከተማ መሆኗን አውስተው፤ በቀጣይም በመከባበር አብሮነታቸውን አስጠብቀው እንደሚያስቀጥሉ ተናግረዋል።


 

በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የብልጽግና ፓርቲ  የጅማ ከተማ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ለታ አሸብር ባደረጉት ንግግር፤ ጅማ  የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች  ተዋደውና ተዋልደው የሚኖሩባት ከተማ ናት ብለዋል።

ከጥንትም ከንጉሱ አባጅፋር ዘመን ጀምሮ ጅማ ብሔር ብሔረሰቦች ተከባብረው የኖሩባት የብዝሃነት ተምሳሌት ስለመሆኗም ጠቅሰዋል።

እኛ ኢትዮጵያዊያን የባህል፣ የቋንቋና የአኗኗር ዘይቤ ብዝሀነትን ተቀብለንና ውበት አድርገን ወንድማማችነትን አስቀጥለን በሰላም የመኖር እሴታችንን ማጎልበት አለብን ብለዋል።

በበዓሉ አከባበር ስነ-ስርዓት ላይ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ የመከላከያና የፖሊስ አባላትን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ  ክፍሎች ተካፍለዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ 18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል  ህዳር 29 ቀን 2016 ዓ.ም በሶማሌ ክልል ጅግጂጋ  ከተማ እንደሚከበር ቀደም ብሎ ተገልጿል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም