በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በበጋ መስኖ 146 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 20/2016 (ኢዜአ) ፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የደረሱ ስብሎችን ከመሰብስብ ጎን ለጎን በበጋ መስኖ 146 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።

የኢዜአ ሪፖርተር በማዕከላዊ ኢትዮጰያ ክልል የግብርና እንቅስቃሴን በሚመለከት በተለይም በሀላባ፣ ስልጤ እና ሌሎችም አካባቢዎች የመስክ ምልከታ አድርጓል።

በመስክ ምልከታውም አርሶ አደሮቹ የደረሱ ሰብሎችን ከመሰብሰብ ጎን ለጎን ለበጋ መስኖ ልማት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን አረጋግጧል።


 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አህመድ ሀቢብ፤ በክልሉ በበልግ እና በመኸር እርሻ 491 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች መልማቱን ገልጸዋል።

ከልማቱም ከቅመማ ቅመም በርበሬና ሮዝመሪ ከ41 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት የሚሰበሰብ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ በ 177 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተዘራና የደረሰ ሰብል የተሰበሰበ ሲሆን ከዚህም ከ8 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ማግኘት ተችሏል ብለዋል።


 

ከ150 በላይ ኮምባይነሮችን ለምርት ስብሰባ መዘጋጀት መሰብሰብ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

በክልሉ የደረሱ ሰብሎችን ከመሰብሰብ ጎን ለጎን ለበጋ መስኖ ልማት እየተደረገ ባለው 146 ሺህ ሄክታር መሬት የሚለማ መሆኑንም ገልጸዋል።

በስልጤ እና ሃላባ ዞኖች ካነጋገርናቸው አርሶ አደሮች መካከል አህመድ ውሃረብ እና አብዱሰላም ከድር የደረሱ ሰብሎችን በኮምባይነር ጭምር እየሰበሰቡ መሆኑን ተናግረዋል።

በኮምባይነር ምርቱን መሰብሰብ መቻሉ ለፍጥነትና የምርት ብክነትን በማስቀረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።፡

በስልጤ ዞን የምስራቅ ስልጤ ወረዳ አርሶ አደሮች፤ ለበጋ የመስኖ ልማት የምርጥ ዘር እና የግብአት አቅርቦት መሟላቱን ጠቅሰው ዘንድሮ ካለፈው ዓመት የተሻለ ምርት ለማግኘት ዝግጅት አድርገናል ብለዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም