ቀጥታ፡

የአፍሪካ መድኃኒቶች ኤጀንሲን ለማቋቋም የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ጸደቀ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 20/2016 (ኢዜአ) ፦የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአፍሪካ መድኃኒቶች ኤጀንሲን ለማቋቋም የቀረበውን የስምምነት ማዕቀፍ አፀደቀ።

የኤጀንሲው መቋቋም የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት ዜጎች ጥራቱ፣ ደህንነቱና ውጤታማነቱ የተረጋገጠ መድኃኒት እንዲያገኙ ያስችላል ተብሏል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 7ኛ መደበኛ ስብሰባው የአፍሪካ መድኃኒቶች ኤጀንሲን ለማቋቋም የወጣውን የስምምነት ረቂቅ አዋጅ ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ ላይ ውይይት አድርጓል።

በምክር ቤቱ የጤና ማኅበራዊ ልማትና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቀሰሙ ማሞ፤ ባቀረቡት የውሳኔ ሀሳብ ሪፖርት የኤጀንሲው መቋቋም ወሳኝ መሆኑ ተመላክቷል።

ኤጀንሲው እንዲቋቋም ኢትዮጵያ ስምምነቱን መፈረሟ በአፍሪካ የመድኃኒት ቁጥጥር አሠራር ሥርዓቶች ላይ ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት እንዲኖር የራሷን ሚና ትጫወታለች ብለዋል።

ለኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የቴክኒክ ድጋፎችን ለማድረግ የኤጀንሲው መቋቋም እገዛ የሚያደርግ መሆኑም ተነስቷል።

በመሆኑም ምክር ቤቱ የአፍሪካ መድኃኒቶች ኤጀንሲን ማቋቋም የሚያስችለውን ስምምነት ረቂቅ አዋጅ የውሳኔ ሀሳብ ተቀብሎ በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል።

በተያያዘ ዜና ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከህትመት ባለፈ በመልቲ ሚዲያ ዘዴዎች ላይ እንዲሳተፍ የሚያስችለውን የተሻሻለ የማቋቋሚያ አዋጅ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።

ድርጅቱ የህትመት ሥራ የካበተ ልምድ ያለው ቢሆንም ወቅቱ ከሚጠይቀው ፍጥነትና ተወዳዳሪነት አኳያ በተለያዩ የመልቲ ሚዲያ ማሠራጫ ዘዴዎች መሳተፍ ተገቢ መሆኑ ተነስቷል።

በምክር ቤቱ የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቱ አለነ፤ ድርጅቱ ከህትመት ባለፈ በመልቲ ሚዲያ ዘዴዎች ላይ ቢሳተፍ ለአገር ገፅታ ግንባታ የሚያበረክተው ሚና የጎላ ይሆናል ብለዋል።

የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው እየዘመነ መምጣቱን ተከትሎ የህትመት ሚዲያው እየተፈተነ በመሆኑ አማራጮችን መጠቀም ተገቢ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ልምድ ባካበተበት የህትመት ሥራ ቢቀጥል የሚልም ከምክር ቤቱ አባላት በጥያቄ መልክ ተነስቷል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ እውነቱ በማብራሪያቸው አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የህትመት ዘርፋ ተፈላጊነትና ተወዳዳሪነት እየቀነሰ በመምጣቱ ገቢ ለማመንጨትና ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል አማራጭ መቅረቡ ተገቢ መሆኑን ገልፀዋል።

የመንግሥት የፋይናንስ ንብረት አስተዳደር መርሆዎችን የተከተለ የራሱን አሠራር እንዲዘረጋም የተሻሻለው የማቋቋሚያ አዋጅ ይፈቅዳል።

ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ዳኛ በሆኑት ጌታነህ ስማቸው ስንብት ላይ ከፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር ዕይታ ለሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም