በብዝሃነት ላይ የተመሠረተ ወንድማማችነትን ማጠናከር ለኢትዮጵያ አንድነት መጽናት ትልቅ ሚና አለው

127

ሚዛን አማን፤  ኅዳር 20/2016 (ኢዜአ) ፡-  በብዝሃነት ላይ የተመሠረተ ወንድማማችነትን ማጠናከር ለኢትዮጵያ አንድነት መጽናት ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ መቱ አኩ ተናገሩ።

"ብዝሃነትና ዕኩልነት ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ 18ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በክልሉ ቴፒ ከተማ እየተከበረ ነው።

የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ መቱ አኩ እንዳሉት፤ በዓሉ የተለያዩ ብሔረሰቦች በጋራ መድረክ ተገናኝተው እሴቶቻቸውን የሚለዋወጡበት የኢትዮጵያዊነት ዓርማ ነው።

እንደ ሀገር ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ለማጎልበት ብዝኅነት ላይ የተመሠረተ ወንድማማችነትን ማጠናከር አስፈላጊ ነው፤ ብለዋል።

የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበር አንድነታችንን ከማጠናከር ባለፈ በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የእስካሁን ተሞክሮዎች የሚፈተሹበት የአንድነት መገለጫ መድረክ መሆኑን አስረድተዋል።

ለብዝሃነት እውቅና መስጠት እና ሕገ መንግስታዊ ዋስትናን ማረጋገጥ የሁሉም አካላት ኃላፊነት መሆኑን ጠቅሰው ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት መጎልበት በጋራ መረባረብ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በብሔር ብሔረሰቦች ልዩነት ውሰጥ ባለ ኅብረ ብሔራዊ  አንድነት የምትደምቅ ሀገር ነች ብለዋል።

በንግግራቸውም "የኔ ብሔር ብቻ" የሚል አስተሳሰብ ለኢትዮጵያ የማይጠቅም መሆኑን ገልጸው ሁሉም ብሔረሰቦች በጋራ ሀገራቸው እኩል ዕድል እንዳላቸው ተናግረዋል።

''ከሁሉም ብሔረሰቦች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን ከሰራን ለክልሉ ዕድገት ብሎም ለሀገር ከፍታ ጉልህ አሻራ የማሳረፍ ዕድል አለን'' ነው ያሉት።

በቴፒ ከተማ እየተከበረ ባለው 18ኛው ክልል አቀፍ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ብሔረሰቦች ተወካዮች እና የዞን እንዲሁም የክልል ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም