በዓሉ የኢትዮጵያውያንን ህብረብሔራዊ አንድነት፣ እኩልነትና ወንድማማችነት አጉልቶ ያሳየ ነው- ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ

151

ሰመራ፤  ህዳር 20/2016 (ኢዜአ) ፦ የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል የኢትዮጵያውያንን ህብረብሔራዊ አንድነት፣ እኩልነትና ወንድማማችነት አጉልቶ ያሳየ ነው ሲሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ።

በአፋር ክልል ደረጃ 18ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል በሰመራ ሎጊያ ከተማ በዛሬው ዕለት ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ የተገኙት የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በዓሉ የኢትዮጵያውያንን ህብረብሔራዊ አንድነት ከማጠናከር ባለፈ በወንድማማችነት ላይ የተመሰረተ እኩልነትን አጉልቶ ያሳየ ነው።


 

እንደ አቶ አወል ገለጻ፣ ከአገራዊ ለውጡ ወዲህ የአፋር ህዝብን በውሳኔ ሰጪነት ያካተተ ሥርዓት በመፈጠሩ ክልሉና ህዝቡ ከአጋር ወጥቶ በአገራዊ አንድነት የጎላ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

ላለፉት ዓመታት የተከበረው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል የአፋር ህዝብ ከሌሎች ወንድሞቹ አብሮነትና እኩልነትን እንዲያጠናክር ከማድረግ ባለፈ ህብረብሔራዊ አንድነቱን ለማጎልበት እንዳስቻለውም ተናግረዋል።


 

የአፋር ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ አሲያ ከማል በበኩላቸው፣ በዓሉ አብሮነትን ከማጠናከር ባለፈ ብዝሃነት ጎልቶና ደምቆ የሚታይበት ነው ብለዋል።

ህብረብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ዛሬ በክልል ደረጃ የተከበረው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ቀደም ባሉ ቀናት በዞንና ወረዳ መዋቅሮችና የተለያዩ ተቋማት ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ፣ የፌዴራል እና የአፋር ክልል ፖሊስ አባላት እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ከፍሎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም