የአብሮነት እሴቶችን በማጠናከር ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ ልንሰራ ይገባል- አቶ ኡሞድ ኡጁሉ - ኢዜአ አማርኛ
የአብሮነት እሴቶችን በማጠናከር ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ ልንሰራ ይገባል- አቶ ኡሞድ ኡጁሉ
ጋምቤላ፤ ህዳር 20 / 2016(ኢዜአ) ፡- የአብሮነትንና የወንድማማችነት እሴቶችን በማጠናከር ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ ልንሰራ ይገባል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ።
''ብዝሃነትና እኩልነት ለአገራዊ አንድነት'' በሚል መሪ ሀሳብ 18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በክልል ደረጃ በኢታንግ ልዩ ወረዳ በድምቀት ተከብሯል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በክብረ በዓሉ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ከለውጡ ወዲህ የክልሉን ህዝብ የሰላምና የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል።
የበዓሉ መከበር የብዝሃነት እሴቶችን ከማስተዋወቅና ከማስረፅ ባሻገር አንድነትንና ወንድማማችነትን ለማጽናት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
የጽንፈኝነት አስተሳሰቦች በጋራና በቁርጠኝነት መታገል እንደሚገባ አመልክተው፤በዓሉን ስናከብርም የህዝቦችን አንድነትና አብሮነትን ለማፅናት ቃል የሚታደስበት ዕለት ጭምር ነው ብለዋል።
የአብሮነትን እሴቶችን በማጠናከር ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ ልንሰራ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የኑሮ ውድነትን ጨምሮ ሌሎችም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍትሄ በመስጠት አገሪቱ ለተያያዘችው የብልጽግና ጉዞ መሳካት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የክልሉ ምክር ቤት አፈ -ጉባኤ ወይዘሮ ባንቻየሁ ድንገታ በበኩላቸው፤ በዓሉ በየዓመቱ እንዲህ በአደባባይ መከበሩ የህዝቦችን አንድነትና አብሮነትን የሚያጠናክር ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህልና እሴቶቻቸውን እንዲያስተዋወቁና ልምድ እንዲለዋወጡ በዓሉ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
የበዓሉ መከበር ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በህገ መንግስቱና በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ዙሪያ የተሻለ ግንዛቤ እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።
በዓሉ በክልሉ ለተከታታይ አምስት ቀናት በተለያዩ መርኃ-ግብሮች ሲከበር የቆየ ሲሆን ፤ በዛሬ የማጠቃለያ ስነ-ስርዓት ላይ የተለያዩ ባህላዊ ጭፈራዎች፣ ትርኢቶችና የደም ልገሳ መርሃ ግብሮች ተከናውነዋል።