ለዜጎች እንግልት ምክንያት የሆኑ የብልሹ አሰራር ችግሮችን በዘላቂነት መፍትሄ መስጠት ይገባል - ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
ለዜጎች እንግልት ምክንያት የሆኑ የብልሹ አሰራር ችግሮችን በዘላቂነት መፍትሄ መስጠት ይገባል - ቋሚ ኮሚቴው
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 20/2016 (ኢዜአ) ፦በተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ የዜጎች የምሬትና እንግልት ምክንያት የሆኑ የብልሹ አሰራር ችግሮችን በዘላቂነት መፍትሄ መስጠት እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ሥነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽንን የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድና የሩብ ዓመት የስራ አፈፃጸሙን ገምግሟል።
የሥነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሳሙኤል ዑርቃቶ፤ በሪፖርታቸው ሙስናን ለመከላከል ሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታን ታሳቢ በደረገ መልኩ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ስጋት የሆነውን የሙስና ወንጀል በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።
ለዚህም ከፌደራል፣ ከክልልና የከተማ አስተዳደር ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰሩ ያሉ በርካታ ተግባራት መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
በ2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በአስቸኳይ ሙስና መከላከል ስራ በ92 ጥቆማ 812 ሚሊየን ብር፣ ከ8 ሺህ ዶላር በላይ እና 1 ነጥብ 9 ሚሊየን ካሬ ሜትር የከተማና ገጠር የመሬት ሃብቶችን ከምዝበራ ማዳን ተችሏል ብለዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በሪፖርቱ በጥንካሬ የተጠቀሱ ተግባራትን በማስቀጠል በክፍተት የተነሱትን በፍጥነት ለማሻሻል መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የመንግስትና የህዝብ ሃብትን ከምዝበራ ለማዳን ኮሚሽኑ እያከናወነ ያለውን ስራ አድንቀው፤ በቀጣይም የተጠናከረ ቁጥጥርና ተጠያቂነትን እንዲሰፍን እንዲሰራ አመላክተዋል።
የኮሚሽኑ የስራ ኃላፊዎችም ከቋሚ ኮሚቴ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በተለይም የበጀት እጥረትና የሰራተኛ ፍልሰት የጸረ-ሙስና ትግሉ እንቅፋት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ምክትል ኮሚሽነር እሸቴ አሰፋ፤ የሙስና ተጋላጭነት አመላካች የጥናት ውጤት በማስቀመጥ ከተቋማት ጋር የህግ ማስከበር ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሚሽነሩ ዶክተር ሳሙኤል ዑርቃቶ በበኩላቸው የሙስና ወንጀልን ለመከላከል ከመገናኛ ብዙኃን፣ ከኦዲት መስሪያ ቤትና ሌሎችም ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በምክር ቤቱ የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አዝመራው አንደሞ፤ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሚና ካላቸው የፍትሕ ተቋማት ጋር በቅንጅት በመስራት የሙስና መከላከል ስራን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ እውነቱ አለነ፤ የሙስና ትግል ሃብት፣ ስልጣንና ጠንካራ ሰንሰለት ካላቸው አካላት ጋር መጋፈጥን የሚጠይቅ በመሆኑ ብዙ ጥረትና ስራ የሚጠይቅ መሆኑን አመላክተዋል።
ዜጎች በመንግስት ተቋማት በሚፈልጉት አገልግሎት የሚያጋጥሟቸው የሙስና እጅ መንሻ ወንጀሎች አምርሮ በመታገል አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የፌደራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በ2022 ከሙስና የፀዳች እና የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ዓላማ ይዞ እየሠራ መሆኑ ይታወቃል።