የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን በአፍሪካ ቀንድ ተጨማሪ የ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዮሮ አስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን በአፍሪካ ቀንድ ተጨማሪ የ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዮሮ አስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 20/2016(ኢዜአ):- የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን በአፍሪካ ቀንድ ለተከሰተው የጎርፍ አደጋ ተጨማሪ የ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዮሮ አስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ተጨማሪ ድጋፍ የሚያደርገው በሶማሊያ፣ በኢትዮጵያ እና በኬንያ በተከሰቱ የጎርፍ አደጋዎች ለተጎዱ ወገኖች መሆኑን የአውሮፓ ሲቪል ጥበቃ እና የሰብአዊ እርዳታ ስራዎች (ECHO) ትናንት ባውጣው መግለጫ አስታውቋል።
ኮሚሽኑ በመግለጫው እንዳመለከተው፤ በሶማሊያ በአሁኑ ወቅት በተከሰተው የጎርፍ አደጋ በተለይም በጁባ ወንዝ ተፋሰስ አካባቢ ለሚገኙ ዜጎች የ2 ሚሊዮን ዮሮ ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚደረግም አመልክቷል።
ይህም የገንዘብ ድጋፍ በሶማሊያ በቅርቡ በኤልኒኖ ምክንያት በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ለተጎዱ እና ለተፈናቀሉ ሰዎች ከዚህ በፊት ከተመደበው 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዮሮ ሰብአዊ እርዳታ በተጨማሪ የተሰጠ ነው ብሏል መግለጫው።
ኮሚሽኑ በኢትዮጵያም በጎርፍ ለተጎዱ አካባቢዎች 1 ሚሊዮን ዮሮ ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጾ፤ ድጋፉም ጎርፉ ጉዳት ባደረሰባቸው አካባቢዎች መጠለያ ለመሥራት፣ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ለማከፋፈል፣ የውሃ ማጣሪያ እና ለህክምና አገልግሎት እንደሚውል አስታውቋል።
የገንዘብ ድጋፉ በሶማሌ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች በአውሮፓ ህብረት የአደጋ ጊዜ ምላሽ ከጎርፉ በፊት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ለመሥራት ከተሰጠው የ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዮሮ አፋጣኝ እርዳታ በተጨማሪ የተሰጠ መሆኑን ኮሚሽኑ አመልክቷል።
ይህም በቅርቡ በኢትዮጵያ ለተከሰተው የጎርፍ አደጋ ምላሽ አጠቃላይ የአውሮፓ ህብረት ያደረገውን የገንዘብ ድጋፍ ወደ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዮሮ እንደሚያሳድገው መግለጫው አመልክቷል።