"ድሽታ ግና'' የኣሪዎች የምስጋናና የምርቃት በዓል!

በጣፋጩ ሰለሞን (ኢዜአ)

በኦሞ ሸለቆ አካባቢ በማጎ ብሔራዊ ፓርክ አቅራቢያ የሚገኙት አሪዎች በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ ''ኣሪ ኣፍ'' ወይም ''ኣሪኛ'' የተሰኘ የመግባቢያ ቋንቋም አላቸው፤ ከኦሞቲክ የቋንቋ ነገድ ይመደባል። የኣሪ ማህበረሰብ የኢኮኖሚ መሰረት ጥምር ግብርና ሲሆን፤ አካባቢውም ቆላ፣ ደጋ እና ወይና ደጋ የአየር ጠባይ አለበት። ኣሪዎች የቤት አሰራራቸው፣ የሙዚቃ ጥበባቸው፣ የአጨፋፈር ስልታቸው፣ አለባበስና አጋጌጣቸው እጅግ ማራኪና የቱሪስት ቀልብን የሚስብ ነው።

እግር ጥሎት ወደ አካባቢው ያቀና እንግዳ ባይተዋርነት እንዳይሰማው የሚያደርገው የኣሪዎች የእንግዳ አቀባበል ባህል የሚደነቅ ነው። አሪዎች ለቤታቸው እንግዳ የሆነን ሰው ''አቦቶ፤ ደኣይቶ'' - ውይ በሞትኩልህ! እንደማለት ነው እያሉ ደረታቸውን እየደቁ ይቀበላሉ። ለእንግዳው አርደውና አብልተው ሲመሽ ደግሞ እግሩን አጥበው አልጋቸውን ለቀው መሬት አንጥፈው ያስተኛሉ።

የራሳቸው የጊዜ ቀመር አቆጣጠር ያላቸው ኣሪዎች ''ሎንጋ'' በተሰኘው የታህሳስ ወር አሮጌውን ዓመት ሸኝተው አዲሱን ዓመት ይቀበላሉ። ይሄው አዲስ ዓመታቸው ደግሞ ''ድሽታ ግና'' የሚል መጠሪያ ያለው ትልቅ ዓመታዊ ክብረ በዓላቸው ነው።


 

የኣሪ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የባህል፣ የታሪክ፣ የቅርስ ጥናትና ልማት የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ዳኜ ገብሬ እንደሚሉት የአዲስ ተስፋና ወንድማማችነት ተምሳሌት የሆነው ድሽታ ግና በማህበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው በዓል ነው። የብሔረሰቡ የዘመን መለወጫ የሆነው የ"ድሽታ ግና" በዓል የሁለት ቃላት ጥምር ሲሆን ''ድሽታ'' ምስጋና "ግና'' ደግሞ ምርቃትን ይወክላል።

የ"ድሽታ ግና" በዓል አርሶ አደሩ የዘራው ዘር ፍሬ አፍርቶ ጎተራው፣ ከብቶች ተዋልደው ጋጥ ሲሞላና ቤቱ በበረከት ሲትረፈረፍ ፈጣሪን የሚያመሰግኑበት፤ በባህል መሪዎች ቡራኬ የሚሰጥበት ታላቅ የምስጋናና የምርቃት በዓል ነው። በባህሉ መሰረትም ወደ አዲሱ አመት ቂምና ቁርሾን ይዞ መሻገር አይቻልም። ስለዚህ ከበዓሉ በፊት በዳይና ተበዳይ "ይቅር" ተባብለው ቂም በቀልን ከአሮጌው ዓመት ጋር ሸኝተው በፍቅር አዲሱን ዓመት እንደሚቀበሉ ነው አቶ ዳኜ የሚናገሩት፡፡

በዚህም መሰረት አንድ የኣሪ ማህበረሰብ አባል በዓሉ ከመድረሱ በፊት "በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ያስቀየምኩት ካለ" በሚል በየቤቱ እየተዟዟረ ይቅርታ ይጠይቃል። በዚህ አጋጣሚ ምናልባት እስከ ህይወት መጥፋት ድረስ የሚደርስ በደል ከተፈፀመ በዳዩ ሽማግሌ ልኮ ፀፀቱን ገልፆ ተበዳይን ተማፅኖ ይቅርታ ይጠይቃል፤ ይቅርታም ይደረግለታል። በየቤቱ ይቅርታ የሚጠይቅበት ምክንያት ቂምና ቁርሾ ወደ አዲሱ ዓመት መተላለፍ ስለሌለበት ነው። ቂምና ቁርሾ በውስጡ ይዞ በዓሉን የሚያከብር አሊያም የበዓል ድግስ ደግሶ ጎረቤት ጠርቶ ማብላት በብሔረሰቡ ዘንድ በጥብቅ የተከለከለ እንደሆነ አቶ ዳኜ ይገልፃሉ።

አንድ የኣሪ ማህበረሰብ አባል ዕርቅ ከፈፀመ በኋላ "አርሼ ጥሩ ምርት አግኝቻለሁ፤ ነግጄ አትርፊያለሁ፣ ከብቶቼ ጋጣ ሞልተውልኛል፣ ቤቴ በበረከት ተትረፍርፏል" ሲል ካገኘው ላይ ቀንሶ ድል ያለ ድግስ ይደግሳል። ድግሱ የተራበውን በማብላት፣ የተቸገረውን በመጎብኘት ፈጣሪ ላደረገላቸው በጎ ነገር ከሌሎች ጋር አብሮ ማዕድ በመቋደስ ለፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርብበት እንደሆነም አቶ ዳኜ ይናገራሉ።


የ"ድሽታ ግና" በዓል እሸት የሚቀመስበት ነው። በበዓሉ ዕለት የኣሪ ባላባቶች እሸቱን፣ ወተቱን፣ ማሩን ከቀመሱ በኋላ መጪው ዘመን የተባረከ፣ የጥጋብ፣ የሰላምና የጤና እንዲሆን ይመርቃሉ። የሰላምና የአብሮነት እንዲሁም ያለፈውን ዘመን በመተው በአዲስ ተስፋ እጅ ለእጅ በመያያዝ ወንድማማችነትን በማጠናከር ሰርቶ በመለወጥ እና ለሌላው መትረፍን ጭምር የሚያበረታታ በዓል ነው።

የብሄረሰቡ ተወላጅ የሆኑት አቶ ፍቃዱ ጋሲ በእንደሚናገሩት፤ የ"ድሽታ ግና" በዓል የፍቅር፣ የአንድነትና የይቅርታ አስተምህሮ ያለው  አብሮነትን የሚያጠናክር ነው። በዓሉ የተጣላውን የሚያስታርቅ የተራራቀውን የሚያቀራርብ በመሆኑ በየዓመቱ በጉጉት ይጠበቃል። የዕድገትና ለውጥ መሰረት ጭምር ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

የዘንድሮውን የ"ድሽታ  ግና" በዓልም አብሮነትን፣ አንድነትን፣  መረዳዳትን በሚያጎላ ብሎም የባህሉን እሴት በጠበቀ መልኩ ለማክበር መዘጋጀታቸውን አቶ ፍቃዱ ይገልጻሉ። የ"ድሽታ ግና" በዓል ጠቃሚ ባህላዊ እሴቶች ያሉትና ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ የመጣ ነው። አሁንም በዓሉ ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር በማስተማር ሃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ነው በአጽንኦት የተናገሩት።

የ"ድሽታ ግና" በዓል ከመድረሱ አስቀድሞ እናቶች ከእንሰት እና ከእንስሳት ተዋጽኦ የሚገኙ ለክብር እንግዶችና ለአባ ዎራዎች የሚቀርቡ ባህላዊ ምግቦችን የማዘጋጀት ስራ ላይ እንደሚጠመዱ የገለጹት ደግሞ የብሔረሰቡ አባል ወይዘሮ ደብሪቱ ኣዳዮ ናቸው። ወጣት ሴቶችና ወንዶች ደግሞ ቤት በማስዋብ እና ግቢ በማሳመር ስራ ላይ ይሳተፋሉ። በበዓሉ ወቅትም በቤት ውስጥ የተዘጋጁ ምግቦች በዓይነታቸው ተለይተው ይቀርባሉ። ጥሩ ምግብ ያዘጋጀችና ምግቧ ጣፋጭ የሆነላት ሴት በግጥምና በዜማ ትወደሳለች።

የ"ድሽታ ግና" በዓል "የተጣሉትን በማስታረቅ፣ ከተቸገሩ ወገኖች ጋር ቤት ያፈራውን አብሮ በመቋደስ ፣የታመሙትን በመጠየቅ በጋራ  የምናከብረው ልዩ በዓል ነው" ያሉት ወይዘሮዋ "ድሽታ  ግና" ፍቅር፣ አንድነት እና በጎነት ጎልቶ የሚታይበት ዕለት እንደሆነም ነው የገለጹት።

በድሽታ ግና በዓል "በዕርቅ የማይቋጭ ጥል፣ የማይድን ቁስል፣ የማይሽር ጠባሳ የለም" ብለዋል። በነዋሪው ዘንድም ለዘመናት ለዘለቀው ሰላምና አንድነት እንዲሁም ጠንካራ የስራ ባህል መሰረት ነው፡፡

የኣሪ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ኤሊያስ ቃሾ በበኩላቸው፤ በዓሉ ከኣሪ ማህበረሰብ አልፎ ለመላው ኢትዮጵያዊያን የሚሆን  "በርካታ ጠቃሚ እሴቶችን በውስጡ የያዘ ነው" ሲሉም ይገልጻሉ። "ድሽታ ግና" ሰላም፣  ፍቅር፣ አንድነትን፣ መረዳዳትን እና አብሮነትን  የሚያስተምር ህዝብ ለህዝብ የሚያቀራርብ  ዕሴት ያለው በዓል ነው፡፡ የ"ድሽታ ግና" በአል ከጥንት አባቶቻችን ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ በዓል ቢሆንም የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ በመሆኑ ተደብቆ የኖረ ቱባ ባህል መሆኑን አንስተዋል።

ሃላፊው እንዳሉት የ"ድሽታ ግና" በዓል ከለውጡ ማግስት በመንግስት በተሰጠው ትኩረትና ባገኘው ዕውቅና የአደባባይ በዓል ሆኖ በመከበሩ "የአገር ውስጥና የውጭ አገራት ቱሪስቶች እንዲጎበኙት በር ከፍቷል" ብለዋል። የ"ድሽታ ግና" በዓል እንደ ሌሎች ዕውቅና እንዳገኙ ክብረ በዓላት አድጎ፣ ጎልብቶ እንዲሁም ዕውቅና አግኝቶ ከአገራችን አልፎ የዓለም ቅርስ እንዲሆን የመላ ኢትዮጵያዊያንን እገዛ ያስፈልጋል።

የዘንድሮው የድሽታግና በዓል ''ድሽታ ግና ለዘላቂ ሰላም እና ለፈጣን ልማት'' በሚል መሪ ሀሳብ በዞኑ ሁሉም አካባቢዎች  በድምቀት እንደሚከበር የተናገሩት ደግሞ የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ ናቸው።

በዓሉ "የመተሳሰብ፣ የመረዳዳትና የዕርቀ-ሰላም በመሆኑ የተጣላውን በማስታረቅ፣ የተቸገሩ ወገኖችን በመጎብኘትና ማዕድ በማጋራት ይከበራል" ብለዋል።

ሰላምና ወንድማማችነትን የሚሰብከው "ድሽታ ግና" የአሮጌው ዘመን ማጠቃለያና አዲሱን ዘመን ብስራት ከአጎራባች ዞኖች እና  ከመላው ኢትዮጵያዊያን ጋር ዕሴቱን በጠበቀ መልኩ በአደባባይ በጋራ ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል።

የ"ዲሽታ ግና" ዕሴቶች አገር በቀልና በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው መሆኑን ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው፤ እንደአገር ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲሁም የብልጽግና ጉዞን ለማጠናከር "ለተወጠኑ ግቦች ስኬት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ልንጠቀምበት ይገባል" ብለዋል።

ከወርሃ ህዳር አጋማሽ ጀምሮ ከቤተሰብ እስከ ኣሪ ባላባቶች ቅደም ተከተሉን ጠብቆ የሚከበረው የ"ድሽታ ግና" በዓል ታህሳስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ደግሞ የአዲስ ዓመት ብስራት ይታወጅበታል። በዕለቱ በጂንካ ከተማ በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች በድምቀት ይከበራል።

''ዑሳ ዎም ዣዕሼ !'' እንኳን አደረሳችሁ!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም